ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

23

ደብረብርሃን፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎በርካታ ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ፣ የተሻለ መሠረተ ልማት ለማሟላት እና የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ምዘገባ እያካሄደ መኾኑን የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳር ገልጿል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የከተማውን ዕድገት ተከትሎ የመኖሪያ ቤት ፈላጊ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቤት ፍላጎቱን ለማሟላት ከተናጠል የመኖሪያ ቤት ማኅበራት በተጨማሪ በአማራጭ የጋራ መኖሪያ ቤት መገንባት አስፈላጊ መኾኑ ታምኖበት የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ምዝገባ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤት በውስን ቦታ ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚችል፣ መሠረተ ልማት ለማሟላት ምቹ እና የከተማውን ገጽታ የሚመጥን በመኾኑ ተመራጭ ኾኖ እንዳገኙት ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሚገነባው የመኖሪያ ቤት ሕንጻ ባለ አራት፣ ባለአምስት፣ ባለ ሰባት እና ባለ ዘጠኝ ወለል ያለው መኾኑንም አመላክተዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የማነ ክብካብ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ 18 ዓመት የሞላው በስሙና በትዳር አጋሩ ስም ቤት እና ቦታ የሌለው፣ የቀን ገቢ ያለው ማንኛውም የከተማው ነዋሪ መመዝገብ ይችላል ብለዋል።

የግለሰቦች መረጃ ተጣርቶ ሲጠናቀቅ ለግንባታ የሚውል በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተሰልቶ 20 በመቶ መቆጠብ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ምዝገባው ማስታወቂያው ከወጣ በኋላ ለአስራ አንድ ቀናት ይቆያል ነው ያሉት፡፡

ግንባታውን ባለቤቱ የሚገነባ ሲኾን ከገንዘብ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ሥራ በቀጣይ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የቤት መስሪያ ቦታ እንደሰጠ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕጻናት የተስተካከለ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገት እንዲኖራቸው ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ ጉልህ ድርሻ አለው።
Next articleበሚተካ ደም የማይተካ ሕይወት መታደግ አስደሳች ስጦታ ነው።