ሴቶች ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በእንክብካቤ ላይም እንዲሳተፉ እየተሠራ ነው።

9

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የከተማውን ሴቶች በማስተባበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውኗል። በተከላ መርሐ ግብሩ የተሳተፉት የዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አለምነሽ አብርሃም አካባቢው እንዲለማ፣ አየሩ ተስማሚ እንዲኾን እና ለቀጣዩ ትውልድም እንዲተርፍ አስበው ችግኝ እንደተከሉ ተናግረዋል።

በሁለት ልጆቼ ሥም ሁለት ችግኞች ተክያለሁ ያሉት ወይዘሮ አለምነሽ ችግኝ መትከል ከቤተሰብም አልፎ ለወገን እና ለትውልድ እንደሚተርፍ ገልጸዋል። የተከልኳቸውን ችግኞች ልጆቼን ይዤ በመምጣት እንከባከባቸዋለሁ ነው ያሉት ወይዘሮ አለምነሽ።

ሌላኛዋ የተከላው ተሳታፊ ወይዘሮ ቃልኪዳን መንግሥቱ ችግኝ መትከል ለትውልድ የሚተርፍ በመኾኑ ደስተኛነታቸውን ተናግረዋል።

የተከሉትን ቡና ለመንከባከብም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸው ሌላው የኅብረተሰብ ክፍልም በየአደረጃጀቱ ችግኝ ቢተክል ጠቃሚ እንደሚኾን ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ በክረምት በጎ ፈቃድ ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል እንዱ ችግኝ ተከላ መኾኑን ጠቅሰው የዛሬውን የችግኝ ተከላም የከተማው ሴቶች በአርዓያነት የፈጸሙት መኾኑን ገልጸዋል።

ሴቶች ችግኝ እንዲተክሉ እና እንዲንከባከቡ የግንዛቤ ፈጠራ መሠራቱን ጠቅሰው 37 ሺህ ችግኝ ለመትከል እንደታቀደም ጠቁመዋል።

ሴቶች ባሕር ዳርን አረንጓዴ እና የቱሪስት መስህብ እንዲያደርጉ ታስቦ የሚሠራው ሥራ አካል በመኾን በቀጣይም ችግኞቹ እንዲጸድቁ እንክብካቤ እንደሚደረግ መምሪያ ኀላፊዋ ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ንጉሴ በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል። ኀላፊዋ በሰጡት አስተያየትም “በመትከል ማንሰራራት” በሚለው መሪ መልዕክት መሰረት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ችግኝ እየተከለ መኾኑን ገልጸዋል። ባሕር ዳር አረንጓዴ፣ ውብ፣ የቱሪስት መስህብ እና የኢንዱስትሪ መነኻሪያም እንድትኾን ታልሞ በሚተከለው ችግኝ ሴቶች በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የችግኝ ልማት ፕሮግራሙን ለማሳካት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ ብርሃን በከተማው 3 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ በትኩረት እንዲሠራም ወይዘሮ ብርሃን አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበክልሉ ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመቅረፍ የእናንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
Next articleሕጻናት የተስተካከለ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገት እንዲኖራቸው ጤናማ የአመጋገብ ዘዴ ጉልህ ድርሻ አለው።