በክልሉ ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመቅረፍ የእናንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

29

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለ34ኛ ዙር የመደበኛ እና የአድማ መከላከል ምልምል ሠልጣኝ ፖሊሶች በብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በሥልጠና ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሸነር አበበ ደለለ በወቅታዊ ሁኔታዎች እና በሀሰተኛ ወሬዎች ሳትደናገሩ የፖሊስ ሙያን ወዳችሁ እና መርጣችሁ ስለመጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያደገበት እና የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሪፎርም እያካሄደ ባለበት ወቅት የሚሰጥ ሥልጠና በመኾኑ የተሻለ ሞራልና መነቃቃት ይፈጥራል ነው ያሉት።

በክልሉ ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመቅረፍ እና ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የሠልጣኞቹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። በመምህራን እና በአሠልጣኞች የሚሰጣቸውን ሥልጠና በተገቢው መንገድ መከታተል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የሥልጠናው ዋና አሰተባባሪ ኮማንደር ግዛቸው ከበደ ሠልጣኞች በትምህርትም ሆነ በአካል ብቃት ብቁ እንዲሆኑ መምህራን እና አሠልጣኞች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሠልጣኞችም የሚሰጣቸውን ሥልጠና በወኔ እና በተነሳሽነት በመሠልጠን የአማራን ሕዝብ ለማገልገል ጉጉት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአማራ ክልል ስንት ሄክታር መሬት ታርሷል?
Next articleሴቶች ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በእንክብካቤ ላይም እንዲሳተፉ እየተሠራ ነው።