በአማራ ክልል ስንት ሄክታር መሬት ታርሷል?

16

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎ወቅቱ የእርሻ ነውና አርሶ አደሮች ውሏቸው በእርሻ መሬታቸው ላይ ነው።

አርሶ አደሮች ሥራቸው እንዲቀና የእርሻ ግጥሞችን በቀየው ዜማ እያዋሀዱ እስከ ፀሐይ ግባት ሥራቸውን ይከውናሉ።

በሰሜን ሸዋ ዞን የስያ ደብር ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አስፋው ጠገናው

እሹሩሩ ጎኔ
እሹሩሩ ጎኔ
የበሬን ውለታ፣ የትራክተርን ውለታ እንጫዎት ማታ
እየበላን ንፍሮ በሰፊው ገበታ እያሉ የእርሻ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። እኛም አርሶ አደር አስፋው ጠገናውን ስለወቅቱ ሥራቸው ጠይቅናቸዋል።

ሥለ ክረምቱ ሥራቸውም ነግረውናል። በዘንድሮው የምርት ዘመን ጤፍ፣ ስንዴ እና ባቄላ ለመዝራት መሬታቸውን አርሰው ማዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

ምርታቸውን ከፍ ለማድረግም መሬታቸውን በትራክተር እንዳረሱ እና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። ከአንድ ሄክታር መሬት የተሻለ ምርት እጠብቃለሁም ይላሉ።

አርሶ አደር አስፋው ቀደም ሲል ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ሳይከተሉ እና ግብዓቶችን በአግባቡ ሳይጠቀሙ ያገኙት የነበረው ምርት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን ከአራት ዓመታት ወዲህ በሚጠቀሙት ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እና ግብዓት አጠቃቀም የተሻለ ምርት በማምረት በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓቸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው ለምርት ዘመኑ ስኬታማነት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል።

ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል የእርሻ ሥራ ቀዳሚው ተግባር መኾኑን ጠቁመዋል። ከ556 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን ከ658 ሺህ 026 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል። የታረሰው መሬት ከዕቅድ በላይ መኾኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ20 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሠበሠባል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂ የማገዝ ሥራ ተከናውኗል ያሉት አቶ አበበ በዚህም 74 ሺህ 669 ሄክታር መሬት በትራክተር ታርሷል ብለዋል።

ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 660 ሺህ 825 ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ ከነበረው ማዳበሪያ ጋር ተዳምሮ 781 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሮች መጓጓዙን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

12 ሺህ 718 ኩንታል ምርጥ ዘር ወደ አርሶ አደሮች ማጓጓዝ ተችሏል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ 469 ኩንታል ምርጥ ዘር የአርሶ አደሮች እጅ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል።

የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለ ከኾነና የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት ወቅቱን የጠበቀ ሥራ ከተሠራ ከተያዘው ዕቅድ በላይ የተሻለ ምርት እንደሚመረት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2017/2018 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጿል።

ይህንን ግብ ለማሳካት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወነ መኾኑን የሚገልጸው ቢሮው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እና ግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጓል ብሏል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደገለጹት ክልሉ በዚህ የምርት ዘመን ከፍተኛ የመኸር ሰብል ለማምረት አልሟል። ከታቀደው 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ እስካሁን ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጋው መሬት ታርሷል።

ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ ከነበረው 982 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 474 ሺህ ሄክታር ያህሉ በትራክተር መታረሱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከታረሰው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ቀሪዎቹ ሰብሎች እንደ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ ሰሊጥ እና የመሳሰሉት ለመዝራት በዝግጅት ላይ እንደኾኑም ተናግረዋል።

ምርት እና ምርታማነትን ውጤታማ ለማድረግ ዋናው ሥራ አረም ነው። ይህንን ማነቆ በወቅቱ ለመሻገር የተዘራው ሰብል ከበቀለ ከ21ኛው እስከ 30ኛው ቀን የመታረሚያ ጊዜው በመኾኑ አርሶ አደሮች ይህንን ወቅት ሳያሳልፉ ማሳቸውን ከአረም ማጽዳት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

የግብርና ባለሙያዎችም የሰብሎቹ የመታረሚያ ጊዜ ሳያልፍ በወቅቱ እንዲያርሙ እና ተባይ እንዳይከሰት የማሳ ዳሰሳ ክትትል በማድረግ ለአርሶ አደሮች የምክር እና የሙያ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበትምህርት ቤቶች ገጽታ ማሻሻል እና ግብዓት ማሠባሠብ ሥራ ላይ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።
Next articleበክልሉ ያጋጠመውን የሠላም መደፍረስ በዘላቂነት ለመቅረፍ የእናንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።