
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ሥትራቴጅክ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግሰው መለሰ እንደገለጹት በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢታቀድም በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር እስከ መጋቢት 30/2017 ባለው ጊዜ በሦሥት ዙር መመዝገብ የተቻለው ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ነው።
በተለይም በሦሥተኛው ዙር ምዝገባ የክልሉ ምክር ቤት ልዩ ውሳኔ ጭምር በማሳለፍ በተሠራው የንቅናቄ ሥራ ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል። በርካታ ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ተደርጓል ብለዋል።
በትምህርት ዘመኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ቢሠራም ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ግን ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መለስተኛ እና ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጉዳቱ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰው ጉዳት ጋር ሲደመር ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጹት።
በ2018 የትምህርት ዘመን የመማር ማሥተማር ሥራውን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን የመመለስ እና በሰው ሠራሽም ኾነ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ የመጠገን ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በክረምት ወራት ደግሞ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ማሻሻል፣ ግብዓት ማሟላት፣ የትምህርት ቁሳቁስ የማሠባሠብ ሥራ ይሠራል ብለዋል። ከነሐሴ/2017 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ምዝገባ ይካሄዳል። ለዚህ ደግሞ ወላጆች፣ ተቋማት እና ባለሃብቶች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ያነሱት ኀላፊው ለዚህ ደግሞ ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የንቅናቄ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻል መርሐግብር ባለሙያ አንዱዓለም ጤናው እንደገለጹት ደግሞ በ2018 ዓ.ሰም የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሻሻል ማኅበረሰቡን ባሳተፍ ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በቀጣይም ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የክትትል ሥራዎችን ማጠናከር እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ደግሞ በወቅቱ የመፍታት ሥራ ትኩረት የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። በትምህርት ቤቶች ገጽታ ማሻሻል እና ግብዓት ማሠባሠብ ሥራ ላይ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን