በትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻል ሥራ ላይ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጠየቀ።

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ የእቅድ ትውውቅ ላይ ውይይት አካሂዷል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ስብራት አጋጥሟል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው ችግር ምክንያት ደግሞ በርካታ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ውጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። በ2017 የትምህርት ዘመን ብቻ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን በማሳያነት አንስተዋል።

ግጭቱ የትምህርት ዘርፉን ቢፈትነውም ባለፉት ወራት የተመዘገቡ 40 በመቶ የሚኾኑ ተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታቸው የተጓተቱ ትምህርት ቤቶች እንዲጠናቀቁ ተደርጓል። የምገባ ሥርዓቱም እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ መሠረተ ልማት እና ግብዓት የማሟላት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ተረድተው እንዲያስተምሩ ሥልጠና ለመስጠት ከታቀደው 15 ሺህ መምህራን ውስጥ 82 በመቶ ለሚኾኑት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በዚህ ክረምትም 27 ሺህ ለሚኾኑ የሁለተኛ ደረጃ፣ 15 ሺህ ለሚኾኑ የአንደኛ ደረጃ መምህራን፣ ርእሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ደግሞ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሠጥ ገልጸዋል።

በቀጣይ የተሟላ መማር ማስተማር ሥርዓት እንዲኖር እና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል መንግሥት ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ማኅበረሰቡም ለትምህርት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ ከማስቀጠል ባለፈ እንዲጠብቃቸው አሳስበዋል። ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ሂደት ሁሉን አቀፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleአልማ በማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቪሽን ለዕይታ አቀረበ፡፡
Next articleበትምህርት ቤቶች ገጽታ ማሻሻል እና ግብዓት ማሠባሠብ ሥራ ላይ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።