
ጎንደር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን “ጥንካሬዎቻችን በማስቀጠል እና ጉድለቶቻችንን በማረም ወደ ሁለንተናዊ ስኬት እናመራለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት አብዩ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን ገልጸዋል። ተፈጥሮ በቆየው የጸጥታ ችግር ምክንያት
ከማኅበረሰቡ ባሕል እና እሴት የወጡ ኢ ሰብአዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አንስተዋል። ይህንንም ማውገዝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የድርሻን መወጣት ይገባል ብለዋል።
መድረኩ የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም የነበራቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግን ዓላማ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ሰላም እንዲሰፍን ውይይት ቀዳሚው መፍትሔ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው
አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ላደረጉት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።
ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ እሴትን መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
የጸጥታ ችግሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች እያስከተለ መኾኑም ተገልጿል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በዞኑ የጸጥታውን ችግር ተከትሎ የተከሰቱ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል። የጸጥታ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝም የበኩላቸውን እያበረከቱ መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥትም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ታጥቀው የወጡ አካላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ለማድረግ ረገድ እየሠሩ መኾናቸውን ተገልጿል።
በዞኑ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ከ600ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸው ተነስቷል። በመሠረተ ልማቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎችም አገልግሎቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን