የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት የደንበኞችን ርካታ ለማረጋገጥ ይሠራል።

13

አዲስ አበባ: ሐምሌ 07/2017 (አሚኮ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ ከክልል መዝጋቢ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ጉባኤ እያካሄደ ነው።

ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት አስራ አንድ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር የዘመናት የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ሀገሪቱ አባል በኾነችባቸው የ105ቱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ትብብር ኢትዮጵያውያን በአባል ሀገራቱ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

ሪፎርሞቹ ተግባራዊ መኾን ከጀመሩበት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዜጋ ተኮር ቅንጅታዊ ትብብራዊ ዲጂታል አሠራሮች እና ተግባራዊ በማድረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

የሰው ሃብትን በማልማት እና ስምሪት በመስጠት አሠራርን በማዘመን አደረጃጀትን በማስተካከል የአገልግሎት አሰጣጥን ዜጋ ተኮር በማድረግ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ሪፎርሙ ሲጀመር ከነበረበት 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በ2017 በጀት ዓመት ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ሪፎርሙን በመተግበር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የፓስፖርት አገልግሎት ተሰጥቷል፣ ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የድንበር አገልግሎት እና ለአንድ ሚሊዮን የውጭ ዜጎች አገልግሎት በመስጠት 3 ሚሊዮን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መካሄዱንም አስታውቀዋል።

የ2017 በጀት ዓመት ተስፋ ሰጪ ቢኾንም በ2018 በጀት ዓመት አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የደንበኞችን ርካታ ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት የሚሠራበት ዓመት ይኾናል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።

በጉባኤው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የክልል መዝጋቢ እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ክትትል እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ተናገሩ።
Next articleዛሬ የለገስነው ደም ነገ ለእኛም ነው።