ዓባይ ባንክ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እና የማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት እየሠራ መኾኑን ገለጸ።

15

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ የተመሠረተበትን 15ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የባንኩ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ የኋላ ገሰሰ ዓባይ ባንክ 15ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ደንበኞችን ለማመስገን እና ከባንኩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

ባንኩ ከ15 ዓመት በፊት በ823 አባላት በ125 ሚሊዮን ብር መመሥረቱን አስገንዝበዋል።

አቶ የኋላ አሁን ላይ ባንኩ ከ92 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገቡን እና ከ72 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብም እንዳለው አንስተዋል።

ባንኩ ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማስተላለፍ እንደቻለም ጠቁመዋል።

ዓባይ ባንክ ከ555 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት የተናገሩት ዋና ሥራ አሥፈፃሚው ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ይዞ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ተቋም መኾኑንም አብራርተዋል።

በባለፈው ዓመት ብቻ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኘው ዓባይ ባንክ ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል ብለዋል።

ባንኩ አሁን ላይ ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች በዲጂታል ባንኪንግ በመጠቀም ከ57 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸም ችሏል ነው ያሉት።

ባንኩ በቀጣይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሥራውን ማሳለጥ የሚያስችሉ ባለትልልቅ ወለል ሕንጻዎችን በመገንባት እና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመተግበር ለደንበኞች እርካታ ይሠራል ብለዋል።

ባንኩ ባለፈው ዓመት ብቻ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል ያሉት ዋና ሥራ አሥፈፃሚው በቀጣይም በትምህርት በጤና እና መሰል ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፉን ይቀጥላል ነው ያሉት።

አባይ ባንክ ሐምሌ 7/2002 ዓ.ም ፈቃድ ያገኘ ሲኾን ጥቅምት 25/2003 ደግሞ ሥራ የጀመረበት ነው።

ባንኩ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 25/2018 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብርም ነው የተገለጸው።

ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች አቀባበል ተደረገላቸው።
Next articleየተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ክትትል እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ተናገሩ።