
ባሕርዳር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ ለሰላም እየገቡ ነው።
ከሰሞኑ መንግሥት ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለገቡ ከ467 በላይ ለሚኾኑ ታጣቂዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ ወረሞ ዋጂቱ ንዑስ ወረዳ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች በተከታታይ ቀናት የመንግሥት የሰላም ጥሪ ለተቀበሉ 467 በላይ ለሚሆኑ ታጣቂዎች ሐምሌ 06/2017 ዓ.ም አቀባበል ተደርጓል።
በሀገር መከላከል ሠራዊት የ101ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ማቲዎስ ማደቦ የትም ፣ መቸም ቢሆን ሰላም አሸናፊ ነው ብለዋል። ለሰላም ቅድሚያ በመሥጠት መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ መቻላችሁ ብልህነት መኾኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ ትናንት በጥፋት እና በተሳሳተ መንገድ ላይ የነበሩ ዛሬ ላይ የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ለሰላም እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሕይዎታቸው የተመለሱ ወንድሞቻችን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በጥምረት በመሥራት የሰላም ባለቤት መኾን አባችሁ ነው ያሉት።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ካሳለፍናቸው አስከፊ የሰላም እጦት ችግሮች ትምህርት በመውሰድ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት መልካም መኾኑን አንስተዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ ያጣውን ሰላም መልሶ እንዲያገኘ ላስቻሉ እና ጫካ የነበሩ ወንድሞቻችንን ለተቀበሉ የጸጥታ ኀይሎች ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ከአማራ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች ከነሙሉ ትጥቃቸው መግባታቸው ነው የተገለጸው። በቀጣይ ተከታታይ ቀናቶች አጫጭር የአስተሳስብ እና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን