
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚገነቡ ሁለት የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጎብኝተዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዓባይ ማዶ (ዳግማዊ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ) ያለው የጃይካ ፕሮጀክት ሳይት መሐንዲስ አቶ ውበቱ ልመንህ ፕሮጀክቱ የክፍለ ከተማውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፍላጎት ለ20 ዓመታት እንዲመልስ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በ500 ሚሊዮን ብር የሚገነባው ፕሮጀክቱ በስምንት ወራት የሥራ ቆይታው 39 በመቶ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዚህ ወቅት 44 በመቶ መድረስ የነበረበት ቢሆንም የይዞታ ቦታዎች ቀድሞ አለመለቀቅ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከሚሠራቸው ፕሮጀክቶች ጋር ያለመቀናጀት እና የኮሮናቫይረስ ዕቅዱን እንዳይሳካ እንዳደረጉት ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶክተር) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሟላት ከተጎበኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ ‘‘በአውሥኮድ አማካኝነት የሚሠራው ዝቅተኛ አፈጻጸም አለው’’ ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የወሰን ማስከበር ችግር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ሆነው ለመፍታት እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ፕሮጀክቱ 50 በመቶ መድረስ ነበረበት’’ ያሉት ዶክተር ማማሩ አሁን 25 በመቶ ብቻ መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጃፓን መንግሥት ድጋፍ አማካኝነት በዓባይ ማዶ የሚሠራው ፕሮጀክት ጥሩ አፈጻጸም ቢኖረውም በኮሮናቫይረሱ ምክንያት እየቆመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተቋማት ከ6 ወራት በፊት በውኃ ዘርፍ ተቀናጅቶ ለመሥራት ስምምነት የፈጸሙ ቢሆንም አለመተግበሩን መመልከታቸውን የተናገሩት ዶክተር ማማሩ ‘‘የከፍተኛ የክልሉ መሪዎች ጉብኝት የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት አንድ ርምጃ ነው’’ ብለዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ ‘‘የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ነዋሪ ውኃ እያለው ውኃ የሚጠማ ሕዝብ ነው’’ ብለዋል፡፡ በከተማው ከፍተኛ የውኃ ሀብት ቢኖርም ለኅብረተሰቡ በማድረስ በኩል ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ዓባይ ማዶ እየተሠራ ያለው ፕሮጀክት በተያዘለት የሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ እስከ ለአስርት ዓመታት ማገልግለ እንደሚችል ጥናት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ በጥቁር ውኃ በኩል በአውሥኮድ የሚሠራው ፕሮጀክት ግን ወሰን የማስከበር ችግር ፈተና እንደሆነበት ያመለከቱት ርእሰ መሥተዳድሩ ‘‘በሕገ ወጥ መንገድ የውኃ መስመሮች እንዳይዘረጉ በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ጠንከር ያለ ርምጃ መውሰድ አለበት’’ ብለዋል፡፡
አቶ ተመሥገን በሕገ ወጥ ግንባታዎች ላይ ካሳ እየከፈሉ የሚያስነሱ የሥራ ኃላፊዎች ትክክል አለመሆናቸውን መገምገማቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመከላከል ሕዝቡ እንዲተባበር የጠየቁት ርእሰ መሥተዳደሩ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ባልቻሉ ኃላፊዎች ላይ ርምጃ እንደሚወስዱም አስታውቀዋል፡፡ ለቀጣይ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርን ዘለቂ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በቀን 60 ሺህ ሜትር ኩዩቢክ የውኃ መጠን ያስፈልጋል፡፡ እየቀረበ ያለው ግን 37 ሺህ ሜትር ኪዩቢክ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከሚፈለገው 61 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የጎበኟቸው ሁለት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ሽፋኑ ከ61 በመቶ ወደ 80 በመቶ እንደሚያሳድገው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሪሁን ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ችግሮች ወደከተማዋ ከሚገባው ውኃ 46 በመቶ እንደሚባክን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡