
ጎንደር፡ ሐምሌ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ለትውልድ እዳ አናወርስም” በሚል መሪ መልዕክት የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በጎንደር ከተማ ቀኑ እየታሰበ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰላም አስከባሪ አባላት፣ ወጣቶች እና ሴቶች ተገኝተዋል።
ጎንደር ስለ ፍትሕ ድምጿን ያሰማችበት፣ ለመርህ አልባ አገዛዝ እምቢ ያለችበት ዕለት መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ተናግረዋል።
ስለ መላው ኢትዮጵያውያን እኩልነት ጎንደር ከተማ ድምጿን ያሰማችበት ዕለት መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል።
የትግሉ ችቦ ለኳሽ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ያለፍትሕ ሊያንበረክከው የመጣውን ወራሪ እምቢ በማለት ለሀገር እኩልነት የራሱን ኀላፊነት መወጣቱን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት በርካቶች ሰማዕት ኾነው ሕያው የነጻነት ታሪክ ከትበው አልፈዋል ብለዋል።
አሁን የተገኘውን ነጻነት በመጠበቅ ልማትን በማስቀጠል የዘመኑን ጀግንነት መወጣት ይገባል ነው ያሉት።
የወልቃይት ጠገዴ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ይልማ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ እና ለአማራ ብሎም ለኢትዮጵያውያን የነጻነት አብሪ ቀን ነው ብለዋል።
ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም በአደባባይ ገዝፎ የወጣውን የዘመናት የይገባኛል ጥያቄ የኾነውን የወልቃይት ጠገዴ የአማራ የማንነት ጉዳይ ሕጋዊ እስኪኾን ድረስ ሁሉም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አስረድተዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ የኾኑ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ይዞት የመጣውን ድል ሙሉ በማድረግ በኩል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን