ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የአማራ ሕዝብ የነጻነት መሠረት የተጣለበት ነው።

40

ሁመራ፡ ሐምሌ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዝክረ ሐምሌ 5 በሁመራ ከተማ ተከብሯል። ለ9ኛ ጊዜ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ የአማራ ክልል እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች፣ ከመላው አማራ ክልል በክብር የተጋበዙ እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር የአሥተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት ዛሬ የምናከብረው የጀግንነት፣ የነጻነት እና የክብር በዓል ነው ብለዋል።

በዓሉ ለአማራዊ ማንነት የታገሉ ጀግኖች የሚወደሱበት እና የአማራ ሕዝብ አንድነቱን የሚያጠናክርበት እንዲኾን የሚሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል።

የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ፣ ኅላፊነትን በመወጣት እና የተጀመሩ የዴሞክራሲ እና የነጻነት ዕድሎችን ማስቀጠል ላይ ትኩረት የሚደረግበት እንደኾነም አቶ ጥላሁን ጠቅሰዋል። አቶ ጥላሁን ፈተናዎችን በጋራ በመጋፈጥ እና በመቋቋም መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

“ለመጭው ትውልድ ነጻነትን እንጂ ተሻጋሪ እዳ አናወርስም” ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው። ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የአማራ ሕዝብ የነጻነት መሠረት የተጣለበት መኾኑንም ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል።

ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በጀግንነት እና በጽናት ለዓላማ መቆምን ያሳየበት ታሪካዊ ቀን ነው ያሉት አቶ አሸተ ዛሬም የሐምሌ 5 የአንድነት እና የኅብረት መንፈስ አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።

አቶ አሸተ እክለውም ከስሜት ይልቅ ስሌትን በማስቀደም፣ ከመለያየትም መደራጀትን በመምረጥ ለችግሮች መፍትሄ ፈላጊዎች መኾን ይገባል ብለዋል። አማራዊ ማንነትን እና ነጻነትን ለመጎናጸፍ ምክንያት ለኾነችው ሐምሌ 5 የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

“ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የፈጣሪ ጠባቂነት በእኔ እና በቤተሰቤ ላይ የተገለጠበት ነው” ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው። ያንን ቀን ያለፉት በፈጣሪ እርዳታ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

በዕለቱ በሕወሓት ሲከበቡ በልጆቻቸው እና በባለቤታቸው ላይ በመወሰን ለነጻነት እና ለክብራቸው ቆመው ሞትን በመምረጥ እጅ አልሰጥም ያሉበት ቀን እንደነበርም አስታውሰዋል።

“ብቻዬን የጀመርኩት የዚያ ዕለት ትግል በዙሪያዬ ዕልፍ ትውልድ አስነስቷል” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጎንደር ኃይሉን ያሳየበት፣ አንድነት እና ኅብረት የተገለጠበት ነበር ብለዋል።

ያለፈው አልፏል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ በዚህ ጊዜ ጦርነት በቃኝ የምንልበት በመኾኑ የትኛውም ኃይል ለሰላም እና ለንግግር ራሱን ቢያዘጋጅ የትውልድን ዳግም እልቂት ማስቀረት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ለበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሁመራ ከተማ ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ በበኩላቸው ሐምሌ 5 የትውልዱ የአልሸነፍም ባይነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

ድል እና ነጻነት የተገለጡበት ቀን ነው ያሉት ከንቲባው ይሄንን ነጻነት ዘላቂ ለማድረግ ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን የማዘመኑ ሥራ በሚፈለገው ልክ ተሠርቷል።
Next articleዝክረ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ዘጠነኛ ዓመት በጎንደር ከተማ እየታሰበ ነው።