የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን የማዘመኑ ሥራ በሚፈለገው ልክ ተሠርቷል።

14

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ የኮርፖሬሽኑን የሕንጻ እድሳት፣ የውስጥ አደረጃጀት፣ ምቹ የሥራ ከባቢ ፈጠራን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጎብኝቷል።

የሥራ አመራር ቦርዱ ሠብሣቢ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና የቦርዱ አባላት የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን (ውስኮ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እና ተቋማዊ የሥራ ምቾት ለመፍጠር የተሠራውን (ሪኖቬሽን) ሥራ ነው የጎበኙት።

በጉብኝቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) እና የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ተገኝተዋል።

ከፍተኛ መሪዎቹ የኮርፖሬሽኑን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ለሥራ ምቹ የማድረግ ግንባታዎች እና አሠራሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በተቋሙ መሪዎች እና ባለሙያዎችም ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርዱ የኮርፖሬሽኑን ሥራ አፈጻጸም ሲገመግም የሕንጻው የውጪ ገጽታ መታደስ እና የውስጥ አደረጃጀቱም መስተካከል እንዳለበት አቅጣጫ መሰጠቱን አስታውሰዋል።

ሥራውም ቦርዱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መከናወኑን ገልጸዋል። የኮርፖሬሽኑን ግቢ ማስዋብ ብቻም ሳይኾን ከባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ጋር ተጣጥሞ መገንባቱንም ተናግረዋል።

የውስጥ አሠራሩ ከወረቀት ወደ ዲጂታላይዜሽን ማደጉን የገለጹት ዶክተር አብዱ ጠባብ ክፍሎች ሰፊ እና ምቹ መደረጋቸውንም አንስተዋል።

የሪኖቬሽን እና የዲጂታላይዜሽን ሥራው የሥራ ተነሳሽነትን፣ የሰው ኃይል እና የሃብት አሥተዳደርን የሚያሻሽሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የሪኖቬሽን እና ዲጂታላይዜሽን ሥራው ለሠራተኞች ምቹ ኹኔታ ለመፍጠር፣ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል፣ ፈጣን እና ግልጽ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ፣ ተቋማዊ ደኅንነትን በመጠበቅ ውጤታማ እና ትርፋማ ያደደርጋል ነው ያሉት።

ኮርፖሬሽኑን የማዘመን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ዶክተር አብዱ ሁሴን ሌሎች ተቋማትም መሰል ሥራዎችን ቢፈጽሙ ጠቀሜታው የላቀ መኾኑን ነው ያሳሰቡት።

የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመጠጥ ውኃ፣ በግድብ፣ በዘመናዊ የመስኖ አውታር ግንባታ፣ በጥልቅ እና መለስተኛ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ የተሰማራ የልማት ድርጅት ነው።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበደዌ ሀረዋ ወረዳ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።
Next articleሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የአማራ ሕዝብ የነጻነት መሠረት የተጣለበት ነው።