
ከሚሴ፡ ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዌ ሀረዋ ወረዳ በ2017 በጀት ዓመት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ ካናል፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ ጤና ኬላ እና የገጠር መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ይገኙበታል።
የወረዳው ነዋሪዎች ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ የተገነቡት ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ጥያቄ እንደነበሩ ጠቅሰው አሁን ላይ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸው ያሉባቸውን ችግሮች እንደሚያቃልሉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው እስኪጠናቀቁም በጉልበት እና በገንዘብ የበኩላቸውን ሲወጡ እንደነበርም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የደዌ ሀረዋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሔለም መሐመድ በወረዳው በ2017 በጀት ዓመት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ 32 ፕሮጀክቶችን መገንባታቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡትን 26 ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን አሥረድተዋል።
ቀሪ ፕሮጀክቶች በሁለተኛ ዙር የምረቃ መርሐግብር ይመረቃሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው እስኪጠናቀቁ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ሲወጣ እንደነበረም ጠቁመዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበኩላቸው የወረዳው ሕዝብ እና መንግሥት ተባብረው በመሥራታቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ መቻላቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ትብብራቸውን በማጎልበት ወረዳውን ለማልማት መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተለያዩ ወረዳዎች ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ የተቻለው ሕዝብ እና መንግሥት ሰላምን ለማጽናት ተባብረው በመሥራታቸው መኾኑን ገልጸው በቀጣይም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሰላምን የማጽናት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን