ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

6

ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢዱኬሽን ሰስቴነብል ዲቨሎፕመንት” የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጂት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና መስጫ ክፍሎችን ገንብቶ አስረክቧል።

“ኤዱኬሽን ሰስቴነብል ዲቨሎፕመንት” የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጂት በደብረ ማርቆስ ከተማ ጤና ጣቢያ በተለያየ ምክንያት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት አገልግሎት የሚሰጡ አምስት የሕክምና መስጫ ክፍሎችን ገንብቶ አስረክቧል። ለክፍሎቹ አስፈላጊ የኾኑ የመገልገያ ቁሳቁሶችን ማሟላቱም ተገልጿል።

ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት ከሕመማቸው እስኪያገግሙ የሚያርፉባቸው የመኝታ ክፍሎች፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያገኙበት እና ሌሎችንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚያገኙበት ዕድል የሚፈጥር መኾኑን የኤዱኬሽን ሴስቴነብል ዲቨሎፕመንት ደብረ ማርቆስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሞኝነት ንብረት ገልጸዋል።

ድርጂቱ በማቻከል እና ደንበጫ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኅላፊ ፈንታነሽ አፈወርቅ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ለተለያዩ ጥቃቶች እየተዳረጉ መኾናቸውን ጠቅሰው ለእነዚህ ሴቶች እና ሕጻናት ትኩረት በመስጠት የተከናወነ በመኾኑ አመሥግነዋል።

ጥቃትን በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች ካለባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማውጣት ማኀበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኅላፊ ሐብቴ ወርቁ ድርጂቱ በጤና ተቋሙ የሕክምና መስጫ ክፍሎችን መገንባቱ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎችን በቅርበት ለመከታተል እና ድጋፍ ለመስጠት እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እንደሚሠራም አቶ ሀብቴ ገልጸዋል።

የተገነቡ ክፍሎች የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጂት መሥራት እንደሚጠበቅም መልዕክት ተላልፏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለመጭው ትውልድ ነጻነትን እንጂ ተሻጋሪ ዕዳ አናወርስም።
Next articleበደዌ ሀረዋ ወረዳ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።