የባሕር ዳር ጭስ ዓባይ መንገድ ሥራን የሚያስቆም የወሰን ማስከበር ችግር አለመኖሩን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አስታውቋል፡፡

304

· የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን “የካሳ ክፍያ ገንዘብ የለኝም” በማለቱ ለመሥራት መቸገሩን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገልጿል፡፡

· የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በአንጻሩ “በወቅታዊ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለቅሬታ የሚያበቃ የገንዘብ ችግር የለብኝም” ብሏል፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የባሕር ዳር ጭስ ዓባይ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ ዘገባ የመንገድ ተቋራጩ “የወሰን ማስከበር ካሳ ክፍያ መጓተት ለሥራዬ እንቅፋት ሆኖብኛል” ብሎ ነበር፡፡ አብመድም የሚመለከታቸው አካላትን አነጋግሯል፡፡ የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጥላሁን ፈጠነ “የወሰን ማስከበሩን በባለቤትነት የሚመራው የአስተዳደር ምክር ቤቱ ቢሆንም ምክር ቤቱ በሚሰጠን ኃላፊነት መሠረት የካሳ ግምት እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ ሥራ ሊያስቆም የሚችል ችግር እንደሌለም ከተቋራጩ ጋር መገምገማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በወሰን ማስከበር ምክንያት የዘገየ ሥራ እንደማይኖርም አብራርተዋል፡፡ “ወሰን የተከበረላቸው ነጻ የሆኑ መሬቶችን አስለቅቀንለታል፤ ተቋራጩ ክፍተት ከሌለበት በስተቀር መሥራት ይችላል” ብለዋል፡፡

የዙሪያ ወረዳው ማኅበረሰብም መንገዱን አጥብቆ ይፈልገው ስለነበር አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ፕሮጀክቱ ሥራ እንዳያቆም እየሠራን ነው፤ ያ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል ማለት አይደለም፤ ቀሪ ሥራዎችንም እየተወያየን እንሠራለን” ነው ያሉት ኃላፊው፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ ትልቅሰው እንባቆም ደግሞ የወሰን ማስከበር ሥራ ለመሥራት የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን “በጀት የለኝም” እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለመንገዱ መጓተት አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልና ባለስልጣኑ ይህንን ካስተካከለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን መፍታት እንደሚቻልም አቶ ትልቅ ሰው አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መብት ጥበቃ ወኪል አቶ ገበያው ታመነ የገንዘብ ሚኒስቴር ከወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ አንጻር ገንዘብ አለመላኩ እንጂ የበጀት ችግር እንዳላጋጠመ አስታውቀዋል፡፡ “ከዚህ በፊት እንደመጣልን እንከፍላለን፤ አሁን በወቅታዊ ችግር ምክንያት ገንዘብ አልተለቀቀም፤ የበጀት ችግር ግን እንደ ቋሚ ችግር የሚነሳ አይደለም” ብለዋል፡፡

ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውንና እንደተለቀቀ ክፍያው እንደሚፈጸምም አቶ ገበያው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleኢትዮጵያ እና ሱዳን የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስጀመር ተስማሙ፡፡
Next articleርእሰ መሥተዳደሩ የውኃ መስመሮች እንዳይዘረጉ በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ጠንከር ያለ ርምጃ እንዲወስድ አሳሰቡ፡፡