
ጎንደር: ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ችግኝ ተክለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍቃዱ ተሰማ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ7 ዓመት በፊት መጀመሩን አስታውሰዋል። አረንጓዴ አሻራ ምቹ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል፣ በግብርና መስክ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል። የደን ሽፋንንም ወደ 23 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል። አረንጓዴ አሻራ ከሀገር አልፎ ለዓለም ያለው አበርክቶ ከፍ ያለ መኾኑን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ካሊድ አልዋን በጎንደር ከተማ ተገኝተው በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ልምድ እየኾ መምጣቱንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሀ ደሳለኝ በክልሉ በሁሉም ዞን እና ወረዳዎች የአረንጓዴ አሻራ ተግባራዊ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የፅድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን