
ሰቆጣ: ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ ከተማ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በቀጣዮቹ 90 ቀናት የሚከወኑ ተግባራት የእቅድ ትውውቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የቁሳቁስ ድጋፍ እና የተበላሹ መንገዶችን የመጠገን ተግባር ማከናወናቸውን የሰቆጣ ከተማ ወጣት ፌዴሬሽን ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ደስታ አወጣ ገልጻለች።
ወጣቱ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለውን ተነሳሽነት ያደነቀችው ወጣቷ በተያዘው የክረምት ወቅትም ደም በመለገስ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመጠገን እና የአረንጓዴ አሻራ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገረችው።
የዋግ ኽምራ ወጣቶች ማኅበር ከ21 ሺህ 500 በላይ ወጣቶችን ያቀፈ ሲኾን ባለፉት ዓመታትም በርካታ የልማት እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን መከወናቸውን የወጣቶች ማኅበር ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወጣት በድር ወንድሙ ጠቅሰዋል።
በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራት ተሰማርተው ሲሠሩ እንደነበረ ነው አስተባባሪው የገለጹት። በዞኑ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ41 በላይ ቤቶችን መገንባታቸውን የገለጹት ወጣት በድር በዚህ የክረምት ወቅትም በአረንጓዴ አሻራ እና በትምህርቱ ዘርፍ የተሻለ ሥራ ለመከወን ወጣቶች ዝግጁ ነው ብለዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ሥራ መሠራቱን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ብድራህማን መኮንን ገልጸዋል። ይህም ለ477 ሺህ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያደረገ እንደነበረ ጠቁመዋል።
በዚህ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ121 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ግምቱ ከ164 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልማትን በማልማት ከ500 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅደው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።
ወጣቶችም በበጋው ያሣዩትን የሥራ ተነሳሽነት በማጠናከር በአንድነት ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን በመለየት ተጠናቋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን