የወባ በሽታ ስርጭትን በርብርብ መግታት ይገባል።

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በ2017 ዓ.ም ከ122 ሺህ በላይ የወባ ሕሙማን መመዝገቡን የአሥተዳድሩ ጤና መምሪያ አስታውቋል።

በተመረጡ ቀበሌዎችም የኬሚካል ርጭት ተደርጓል ነው ያለው። በቀጣይም ችግሩ በሚሰፋባቸው አካባቢዎች ያለውን የአልጋ አጎበር በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጸው።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አፀደማርያም አክሊሉ በየቤቱ ወባ ያልታመመበት የቤተሰብ አባል እንደማይገኝ ተናግረዋል።

ወይዘሮ አፀደማርያም አክለውም “በእኛ ግቢ 10 ሰዎች እንኖራለን። አራቱ በወባ በበሽታ የታመሙ ናቸው” በማለት የበሽታውን የስርጭት ማየል የገለጹት። በወባ ታመው የታከሙ ሰዎች በድጋሚ እንደሚታመሙም ነው አስተያዬት ሰጭዋ የተናገሩት።

በተለይ አጎበር በመንግሥት አለመቅረቡ ለበሽታው ስርጭት የበኩሉን አሉታዊ ሚና ተጫውቷል ባይ ናቸው። በግላቸው ገበያ ላይ አጎበር እየገዙ ቢጠቀሙም በኬሚካል ያልተነከረ በመኾኑ የመከላከል አቅሙ ዝቅተኛ ኾኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

ወባን በዘላቂነት ለማጥፋትም ሁሉም ሰው የራሱን ያላሰለሰ ድርሻ መወጣት አለበት የሚሉት ወይዘሮ አፀደማርያም እያንዳንዳችን ግቢያችንን እና አካባቢያችንን ካጸዳን የወባ በሽታን መቆጣጠር ያስችላል ነው ያሉት።

ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ ማለደ ጣሰው የወባ በሽታ እሳቸው በሚኖሩበት ግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ በሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።

ለወባ በሽታ ስርጭት እና መደጋገም ኀብረተሰቡም አስተዋጽኦ እያደረገ ነው የሚሉት አቶ ማለደ የልብስ እጣቢ እና ሌላውንም ቆሻሻ ውኃ ደጅ ላይ ስለሚደፋ ለትንኝ መራቢ ምቹ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፤ እያመቻቸም ይገኛል።

አቶ ማለደ አክለውም “ነዋሪው ቆሻሻውን ደጅ ላይ ሲደፋ የሚያየው ቆሻሻው ከቤቱ መውጣቱን ብቻ ነው። ደጅ ላይ በመደፋቱ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ መደላድል መፍጠሩን አዙሮ አያይም። መሠል ድርጊቶች በየአካባቢው ይዘወተራሉ” ነው ያሉት።

ሁሉም ሰው የአቆረ ውኃን በማፋሰስ እና ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ በተለይ ወባን መከላከል ይገባል ሲሉ መክረዋል።

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ ይዘንጋው መኮንን ወባን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት በመጀመሪያ ሁሉም ሰው አካባቢውን መቆጣጠር እና ማጽዳት አለበት ነው ያሉት።

እንደ መንግሥትም ክረምቱ እየገባ በመኾኑ ያቆረ ውኃን የማፋሰስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። ይሁንና መሠል ሥራዎችን ኅብረተሰቡ በመደራጀት ለወባ መራቢያ ምቹ ሥፍራዎችን የማፋሰስ እና የማድረቅ ሥራዎችን ማከናወን ይኖርበታል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በባሕር ዳር ከተማ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ከፍተኛ የወባ በሽተኞች ቁጥር መመዝገቡን ነው አስተባባሪው የተናገሩት።

122 ሺህ 528 የወባ ታማሚዎች በዓመቱ መመዝገባቸውን አቶ ይዘንጋው ተናግረዋል። በመኾኑም ስርጭቱ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ መከላከሉ ላይ በትኩረት ተሠርቷል።

በከተማዋ በተመረጡ 12 ቀበሌዎችም የወባ መከላከያ የኬሚካል ርጭት መደረጉን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በቀጣይ በሽታው ይበልጥ እንዳይስፋፋ የግንዛቤ ፈጠራው ላይ ይሠራል ነው ያሉት። ሁሉም ሰው ያለውን አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀምም መክረዋል።

በከተማዋ በተመረጡ ወባማ ቀበሌዎች 19 ሺህ የአልጋ አጎበር ለነፍሰ ጡሮች እና ለወላጆች ይከፋፈላል። የመድኃኒት እጥረትም እንደሌለ ጠቁመዋል።

የከተማ አሥተዳድሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሰፋ በበኩላቸው ክረምቱ በመግባቱ መከላከሉ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡ በቤቱ አጎበር መጠቀም ግድ ይለዋል ነው ያሉት። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት ሲዘዋወሩም ኅብረተሰቡ አብሯቸው በመሥራት የበሽታውን መግታት ይገባል ብለዋል። “ወደ ጤና መምሪያው የመጣ አጎበር በመኖሩ ቅድሚያ ማግኘት ላለባቸው እየተሰጠ ነው። በተመሳሳይ አጎበርን ለሌላ ሥራ እያዋሉ የሚገኙትን ግለሰቦች በጋራ መቆጣጠር ይኖርበታል። ‘አጎበር መዋል ያለበት ወባን ለመቆጣጠር ብቻ ነው’ በጠቅላላው የወባ በሽታ ስርጭትን በርብርብ መግታት ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next article“ወባን የገቱ ጠንካራ እጆች”