የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው።

10

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰፊ የእርሻ ልማት ያለበት አካባቢ ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጉልበት ሠራተኞች ለእርሻ ልማቱ ወደ ሥፍራው ያቀናሉ። ብዙ በእርሻ ልማቶቹ በሚገኙ ማደሪያዎች እና በሥራ ቦታዎች ላይ ደግሞ የወባ ወረርሽኝ ይከሰታል።

የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል ደግሞ አሠሪ ባለሃብቶች እና የዞኑ ጤና መምሪያው በጋራ ይሠራሉ።

የወልቃይት ጠገዴ እርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ እና በእርሻ ልማት የተሰማሩት ነጋ ባንትይሁን ባለፈው ዓመት የነበረው የዝናብ መጠን ከፍተኛ ስለነበር የወባ ሥርጭቱም ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።

ዘንድሮ የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት በሠራተኞች መጠለያ እና በማሳዎች ላይ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል። የጉልበት ሠራተኞችን ጤንነት መጠበቅ ግዴታ መኾኑንም ገልጸዋል።

በእርሻ ቦታዎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ የለም፣ የምንጠቀመው ወራጅ እና የደፈረሰ ውኃ ነው ያሉት ባለሀብቱ የወባ እና የሌሎች የውኃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል የውኃ አጋር እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

ዘንድሮ በእርሻ ቦታቸው የጤና ባለሙያ ለመቅጠር በሂደት ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ጊዜያዊ ቦታ ማቋቋመቸውን እና በዞኑ ጤና መምሪያ ዕውቅና የተሰጠው ሐኪም በጊዜያዊነት እንደሚቀጥሩም ተናግረዋል።

የሕክምና ሥራው ምርት ተሰብስቦ እስኪጠናቀቅ እና የጉልበት ሠራተኞች ወደ አካባቢያቸው እስኪመለሱ ድረስ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። ሌሎች ባለሃብቶችም የወባ እና ሌሎች በሽታዎችን የመከላከል ሥራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የሠራተኞችን መኝታ፣ የውኃ አቅርቦት፣ ሕክምና ማመቻቸት ይገባል ነው ያሉት። ሁሉም ባለሀብቶች የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። የዞኑ ጤና መምሪያ ክትትል ማድረግ እንደሚገባውም ገልጸዋል።

በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ባለሃብቶች የጉድጓድ ውኃ ለመቆፈር ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። በሠራተኞቻቸው ላይ ሕመም ሲፈጠር በትራክተር ወደ ሕክምና ተቋማት እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።

የወባ እና የውኃ ወለድ በሽታ ጊዜ የሚሰጥ ስላልኾነ ሠራተኞች ሕመም ሲታይባቸው በፍጥነት መውሰድ ይገባል ነው ያሉት። የዞኑ ጤና መምሪያ ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግ የጠየቁት ባለሃብቱ የመድኃኒት አቅርቦትም በስፋት መቅረብ አለበት ብለዋል። ባለሃብቶች የሚቀርበውን መድኃኒት መግዛት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ስማቸው ግደይ ባለፈው ዓመት የነበረው የወባ ወረርሽኝ ብዙ ነገር አስተምሮን አልፏል ነው ያሉት። ባለፈው ዓመት የነበረውን የወባ ሥርጭት መቀነስ አለብን ብለን እየሠራን ነው ብለዋል።

በተሠራው ሥራም ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት። “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይከላከላሉ” በሚል መሪ መልዕክት አካባቢን የመቆጣጠር ዘመቻ መደረጉንም ተናግረዋል። ዘመቻው ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ እና የነበረውን ሥርጭት የቀነሰ ነው ያሉት ኀላፊው ዘመቻው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡ በክረምት ወቅት ለወባ መራቢያ ምቹ ኹኔታን የሚፈጥሩ አካባቢዎችን ማጽዳት እንዳለበትም ገልጸዋል።

አጎበርን በአግባቡ መጠቀም፣ መመርመር እና መታከም ውጤት እንደሚያመጣ ሁሉ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማጠናከርም ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ሥራ ነው ብለዋል።

አካባቢው በርካታ የጉልበት ሠራተኞች የሚበዙበት በመኾኑ ያን ታሳቢ ያደረጉ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢን የማጽዳት እና የመቆጣጠር ዘመቻ የአንድ ሰሞን ሥራ ብቻ እንዳይኾን በትኩረት እየሠሩበት መኾኑንም ተናግረዋል። የወባ ሥርጭት ላይ በየቀኑ የመረጃ ልውውጥ እና መረጃውን ታሳቢ በማድረግ ግብዓት እንደሚመጣም ገልጸዋል።

ባለሃብቶች በእርሻ ልማታቸው የአካባቢን ቁጥጥር መሥራት እንደሚገባቸው ያነሱት ኀላፊው የአጎበር አጠቃቀምንም ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።

ወደ አካባቢው ለሥራ የሚመጡ የጉልበት ሠራተኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎችም የሕመም ምልክቶች ሲታዩባቸው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ይገባቸዋል ብለዋል። ወባን ብቻ ሳይኾን ሌሎች የውኃ ወለድ በሽታዎች በሠራተኞች መጠለያ ጣቢያ እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ችግሮች ሲያጋጥሙም ለጤና መምሪያው ማሳወቅ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የአጎበር አጠቃቀምን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ እና የአካባቢ መቆጣጠር ሥራን በትኩረት እንዲሠራ አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአዲስ አበባ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
Next articleየወባ በሽታ ስርጭትን በርብርብ መግታት ይገባል።