በአዲስ አበባ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

18

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀርቧል።

በሪፖርቱ ከተነሱ ሀሳቦች መካከል በአሥተዳደሩ የ2017 በጀት ዓመት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ተግባራት ተከናውነዋል።

የከተማዋን የቤት ፍላጎት ለሟሟላት የተለያየ ጥረት እየተደረገ እንደኾነ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች በግለሰብ እና በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በመንግሥት ቤቶችን የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

በዚህም በግለሰብ አልሚዎች 11 ሺህ 260 ቤቶች እና በሪል ስቴት አልሚዎች 30ሺህ 507 ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በኅብረተሰብ ተሳትፎ 8ሺህ 786 ቤቶች መታደሳቸውን እና በመንግሥት ለልማት ተነሺዎች 5 ሺህ 176 ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

ከንቲባ አዳነች በ2017 በጀት ዓመት 55 ሺህ 729 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውንም ነው ያስገነዘቡት።

በሕገ ወጦች የተያዙ 453 የመንግሥት ቤቶች እና 212 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማስለቀቅ ለሚገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደተላለፉም ጠቁመዋል።

በመንገድ ልማት ዘርፍ ረገድ በበጀት ዓመቱ የከተማውን የመንገድ ሽፋን የሚያሳድጉ፣ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጡ፣ የመንገድ ደኅንነቱን የሚያረጋግጡ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ፣ የጉዞ ጊዜን እና ገንዘብን የሚቀንሱ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።

በዚህም 371 ኪሎ ሜትር የአስፓልት፣ 95 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮብል፣ 16 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 107 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ መሠራታቸውን አንስተዋል።

3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ እና የድሬኔጅ ግንባታዎች፣ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በዲጅታል አሠራር፣ በገቢ አሠባሠብ እና መሰል ተግባራት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት መፈጸማቸውንም ከንቲባዋ አንስተዋል።

በቀጣይ የምክር ቤቱ ጉባኤ በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብ፣ አስተያየት እና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

የ2018 በጀትን እና የተለያዩ ሹመቶችን ማጽደቅ የጉባኤው አጀንዳዎች ናቸው።

ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየተፈጠሩ የፀጥታ ስጋቶችን በመቀልበስ በሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ምስቅልቅል መቅረፍ ተችሏል።
Next articleየወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ ነው።