በደብረ ማርቆስ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውኃን ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

8

ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ መንግሥቱ ተፈራ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ከንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ቅሬታ ይነሳባቸው በነበሩ አምስት ቀጣናዎች ላይ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

ያለውን የውኃ ሃብት በፍትሐዊነት ከማዳረስ ጎን ለጎን በ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ ውኃ የማመንጨት ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ከአመልድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አሁን ያለውን የከተማዋን የውኃ ተደራሽነት ከ135 ሊትር በሰከንድ ወደ 156 ሊትር በሰከንድ ሊያሳድግ የሚችል የጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቅቆ አገልግሎት ለማስጀመር የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም 40 ሊትር በሰከንድ ውኃ የሚያመነጩ ጉድጓዶች በክልሉ መንግሥት 176 ሚሊዮን ብር ወጭ ላለፉት ሦሥት ዓመታት እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ይህም አሁን ያለውን የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ከ29 በመቶ ወደ 40 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

እንደ ሥራ አሥኪያጁ ማብራሪያ በከተማ እና በፌዴራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ እነዚህ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ ሲገቡ የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ወደ 50 በመቶ ከፍ ያደርጉታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ የመጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት የውኃ ብክነትን ለማስቀረት በማለም ከፌዴራል ውኃ ልማት ፈንድ ጋር በመተባበር በከተማዋ በ372 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ 109 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የማስፋፊያ እና የማሻሻያ ሥራዎችን ለመሥራት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መጠናቀቃቸውን ሥራ አሥኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የሚቆፈሩ ጉድጓዶች መድረቅ ለዘርፉ ፈተና ኾኖ ቀጥሏል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ችግሩን በዘላቂነት ወደሚፈቱ ፕሮጀክቶች ለማሸጋገር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የጨሞጋ ግድብን በመገደብ የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍም ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት፡፡

ሥራ አሥኪያጁ ለውኃ መገኛ ቦታዎች የሚደረገው እንክብካቤ ደካማ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ለከተማዋ ውኃ አቅርቦት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን የውትርን እና የሰንተራ ተፋሰሶች በአግባቡ ካላመጠበቃቸው በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለእርሻ እና ለሰፈራ እየተጋለጡ በመምጣታቻው በውኃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ተፋሰሶች ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ሥራዎች ተጀምረዋል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ በተፋሰሶች አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ብር በሩሲያ የባንክ ምንዛሬ ውስጥ ተካተተ። የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የኢትዮጵያን ብር በምንዛሬ ዝርዝር ውስጥ አካቷል።
Next articleየተፈጠሩ የፀጥታ ስጋቶችን በመቀልበስ በሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ምስቅልቅል መቅረፍ ተችሏል።