የጤና ጣቢያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስተካከል እየተሠራ ነው።

28

ዝክረ ሐምሌ 5/2008 በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ ታሰቧል።

ሁመራ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ለመጭው ትውልድ ነጻነትን እንጂ ተሻጋሪ እዳ አናወርስም” በሚል መሪ መልዕክት ዝክረ ሐምሌ 5/2008ን ምክንያት በማድረግ በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር የአሥተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት የወልቃይት ጠገዴ ማኅበረሰብ ጀግና መሪዎች ስላሉት ሊኮራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዝክረ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ሲከበር ለዛሬው ብቻ ሳይኾን ለመጭው ትውልድም ተጨባጭ ነጻነትን ለማረጋገጥ ዓላማ በማድረግ ነው ብለዋል።

ቀኑ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ለመላው አማራ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት መሠረት መኾኑን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል።

ቀኑን ሁሌ በማክበር ጀግኖችን ማሰብ እና ማክበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የትብብርን ኅያልነት እና የአንድነት ምስጢር የተገለጠበት፣ የግፍ አገዛዝ የተገታበት፣ ድል የተቀዳጁበት እና ለሀገራዊ ለውጡ ፋናወጊ መኾን የተቻለበት እንደኾነም ነው የጠቀሱት።

“በመራራ ትግል ነጻነታችንን ተጎናጽፈናል፤ “ለመጭው ትውልድም ነጻነትን እንጂ ተሻጋሪ እዳ አናወርስም” ብለዋል።

ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ሲወሳ የአማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ችቦውን በመለኮስ ወደ አንድነት የተሠበሠበበት እንደኾነም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው አስረድተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ እምቢ ለነፃነቴ፣ ለክብሬ እና ለማንነቴ ባይነቱን ያረጋገጠበት ቀን መኾኑን አንስተዋል።

መነሻን ማወቅ መዳረሻን ማወቅ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሐምሌ 5 የነጻነታችን መነሻ መኾኑን በመረዳት መጠበቅ እና ማጽናት ይገባል ብለዋል።

ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ በአዲስ ምዕራፍ የተቀጣጠለበት ነው ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር ዋና ሥራ አሥኪያጅ ገሠሠው ወንድም (ዶ.ር) ናቸው።

በዚህች ቀን በርካቶች ስለያዙት እውነተኛ ማንነት ትግል ሲሉ በግፍ መጨፍጨፋቸውንም የማኅበሩ ሠብሣቢ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀን በኋላ በመላው አማራ እና ኢትዮጵያ በተቀጣጠሉ የእምቢተኝነት ሰልፎች ላይ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ” እያሉ ወጣቶች ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተዋል ብለዋል።

ከዝክረ ሐምሌ 5 መከበር ዋነኛ ዓላማዎች መካከልም እነዚህን የክብር ሰማዕታት መዘከር መኾኑን ነው ዶክተር ገሰሰው ያስረዱት።

የዞኑ አሥተዳዳሪዎች እና መሪዎች ብዙ ጫናዎችን ተቋቁመው እያደረጉት ያለው ትግል የሚደነቅ ነው ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ሕዝቡ ስለማንነቱ ጠንቅቆ እንዲረዳ እና ለነጻነቱ እንዲታገል መጽሐፍ በማሳተም ሳይቀር መሪዎቹ ጥረት ማድረጋቸውን ተሳታፊዎቹ አድንቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጤና ጣቢያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስተካከል እየተሠራ ነው።
Next articleበተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።