የጤና ጣቢያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስተካከል እየተሠራ ነው።

16

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ በሥሩ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በ2017 በጀት ዓመት ያከናዎኗቸውን ሥራዎች እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመገምገም የ2018 ዕቅድ ትውውቅ በተለያዩ መድረኮች አካሂዷል።

በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ የውይይት መድረክ ሲሳተፉ አሚኮ ያገኛቸው ማለደ ጣሰው የሹም አቦ ጤና ጣቢያ አገልግሎት ፈላጊውን ማኀበረሰብ በመልካም ሥነ ምግባር ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን መታዘባቸውን ነገሩን።

ጤና ጣቢያው ክፍሎቹን የሕጻናት፣ የድንገተኛ ሕሙማን፣ የወላዶች እና የተመላላሽ ታካሚዎች በሚል በመለየቱ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አስችሎታል ነው ያሉት።

አቶ ማለደ አክለውም የኀብረተሰቡን ገቢ ያገናዘቡ የሕዝብ መድኃኒት ቤቶች እንዲከፈቱም ጠይቀዋል።

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ አጸደማርያም አክሊሉ የስኳር ሕመም ተከታታይ ታካሚ በመኾናቸው በፈለጉበት ዕለት ወደ ጤና ጣቢያው ሲሄዱ በአግባቡ ሕክምና እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ይኹን እና ሌሊት ሕክምና ፈልገው የሚሄዱ ሕሙማን “ባለሙያ የለም” በሚል እንደሚጉላሉ ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ አጸደ ማርያም ማኀበረሰቡም ጤና ጣቢያውን እንደራሱ እንደሚንከባከበው ተናግረዋል። ለአብነትም የጤና ጣቢያውን ዙሪያ ገባ በዘመቻ ሥራ እያጸዱ መኾናቸውን አንስተዋል።

የሹም አቦ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ልጃለም ጋሻው በውይይት መድረኩ በጤና ጣቢያው የባለሙያ እና የደጋፊ ሠራተኞች ውስንነት በመኖሩ የታካሚዎች የቆይታ ጊዜ እየተራዘመ ነው የሚል ቅሬታ ከኀብረተሰቡ መቅረቡን ተናግረዋል።

በመኾኑም የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ እና አጋር አካላት በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር ችግሩን በፍጥነት ለማስወገድ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ኀብረተሰቡም ጤና ጣቢያውን እንደ ራሱ ሃብት በመቁጠር ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ እና ለመገንባት ቃል መግባቱን ኀላፊው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ የውይይት መድረኩ ዓላማ የጤና ጣቢያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስተካከል እና ማኀበረሰቡ የጤና ጣቢያዎች ባለቤት እንዲኾን የሚያስችል ነው ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በሽታን በመከላከሉ ረገድ ታች ድረስ የቤተሰብ ቡድን በማቋቋም ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ሲስተር ዓለም ስድስት ጤና ጣቢያዎችን ጽዱ እና ለተገልጋዩ ምቹ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ማኀበረሰቡ ወደ ጤና ጣቢያዎች ሲሄድ ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥመው እና በገንዘብ እጦት ሳይሳቀቅ አገልግሎቱን እንዲያገኝ የሚያስችለውን የጤና መድን አገልግሎት ለማስፋት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ይሠራል ብለዋል።

ሲስተር ዓለም 54ሺህ የሚኾነው የማኀበረሰብ ክፍል የጤና መድን ተጠቃሚ መኾኑንም ተናግረዋል።

የግብዓት አቅርቦት መጠንን ከፍ ለማድረግ ከቀይ መስቀል ጋር ውል በመያዝ እንደሚሠራም አብራርተዋል።

የሕዝብ መድኃኒት ቤት መደብር በቅርቡ በፋሲሎ ከተማ እንደሚጀመር ኀላፊዋ ገልጸዋል። በጣና እንዲኹም አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተሞች ላይ ደግሞ የሕዝብ የመድኃኒት ቤት መደብር መገንቢያ ቦታ መረከባቸውን ያስታወሱት ሲስተር ዓለም በቅርቡ ግንባታዎች ይጀመራሉ ነው ያሉት።

ማኀበረሰቡ በላቀ ደረጃ የጤና ጣቢያዎች ባለቤት ኾኖ ዘርፈ ብዙ የድጋፍ ሥራዎችን እንዲያከናውንም ሲስተር ዓለም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአረንጓዴ አሻራ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እየኾነ ነው።
Next articleየጤና ጣቢያዎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማስተካከል እየተሠራ ነው።