
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ እየተከናወነ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመት ላይ ይገኛል፡፡ ዛፎችን መትከል በዋነኛነት ለአካባቢ ጥበቃ እና ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ታስቦ የሚሠራ ቢኾንም ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦውም ከፍተኛ ነው፡፡ ከኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ደግሞ አንዱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው፡፡
የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል በባሕር ዳር ከተማ በችግኝ ማዘጋጀት እና ገጸ ምድር ማስዋብ የሥራ ዘርፍ የተሰማራው ወጣት ንጉሤ ቻሌ አንዱ ነው፡፡ ንጉሤ፣ ዘይድና ጓደኞቹ ሽርክና ማኅበር በሚል ተደራጅተው እየሠሩ ሲኾን ማኅበሩ አራት አባላት ያሉት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለ6 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ነግረውናል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ሥራ የማኅበረሰቡ ችግኝ የመትከል ባሕሉ እያደገ በመምጣቱ ግለሰቦች፣ የግል ድርጅቶች ደንበኞቻቸው እንደኾኑ እና በሥራውም ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሰውዘር ደመላሽ እንደ ንጉሤ ሁሉ ሌሎች ወጣቶችም በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው በተለይም በአረንጓዴ አሻራ ሥራ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
እንደ ኀላፊው ገለጻ በአረንጓዴ አሻራ ዘርፍ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በችግኝ ማዘጋጀት፣ ለምርት በደረሱት ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እና አነስተኛ የደን ውጤቶችን ለግብዓትነት በማቅረብ ዘርፍ ለ3 ሺህ 40 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ወጣቶች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የደን ሽፋንን የሚጨምር በመኾኑ ለወደፊት በተለያዩ ዘርፎች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በደን ውጤቶች አቅርቦት፣ በንብ ማነብ እና የእንስሳት መኖ ላይ ትልቅ የሥራ ዕድል የሚፈጥር መኾኑን አመላክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምኅረት እንደገለጹት በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የሚተከሉ ችግኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አላቸው ነው ያሉት፡፡
የሥራ ዕድል መፍጠር አንዱ ነው፡፡ በአረንጓዴ አሻራ የሥራ ዕድል የሚፈጠርባቸው ዘርፎች በአብዛኛው ችግኝ በማዘጋጀት፣ በደን ዘር መሰብሰብ እና ችግኝ በመትከል መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ለማፍላት የሚኾን የደን ዛፎች ዘር በማሰባሰብ ችግኝ ለሚያፈሉ አካላት ማቅረብ፣ የሚተከሉ ችግኞችን በማዘጋጀት ለሚተክሉ አካላት ለሽያጭ በማቅረብ እና ችግኝ በሚተከልበት ጊዜ በችግኝ ተከላ የሚፈጠር መኾኑን ነው ያብራሩት፡፡ በዚህም እንደ ክልል ለ15 ሺህ 198 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ችግኝ ሲተክል ተፈጥሮን እና ስነ ምኅዳርን ከመጠበቅ ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን