
ከሚሴ: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋጨፋ ወረዳ በ2017 በጀት ዓመት ያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች አስመርቋል።
የደዋጨፋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ ጌታቸው በበጀት ዓመቱ ከ18 በላይ ፕሮጀክቶችን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ወረዳው ገንብቶ ማጠናቀቁን ጠቅሰው በዛሬው ዕለት በመጀመሪያ ዙር ምረቃ 10 ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።
በቀጣይ በሁለተኛ ዙር ምረቃ ቀሪ ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት እንደሚያደርጉ ያሳወቁት ዋና አሥተዳዳሪው በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ወቅት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑ ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ ካናል፣ ጤና ኬላ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎች የማኅበረሰቡ ጥያቄ የነበሩ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበጀት ዓመቱ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ የተቻለበት ዓመት መኾኑን አስረድተዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ከ223 በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይ ቀናት በሁሉም ወረዳዎች ለአገልግሎት ክፍት እናደርጋለን ብለዋል።
በርካታ ፕሮጀክቶችን መገንባት ያስቻለን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምን በማረጋገጡ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በቀጣይም የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ጥረታቸው እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
የደዋጨፋ ወረዳ ነዋሪዎች በበኩላቸው ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት በኾኑ ፕሮጀክቶች መደሰታቸውን ጠቅሰው ተገቢውን ጥበቃ ለፕሮጀክቶቹ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው እስኪጠናቀቁ የበኩላቸውን ሲወጡ እንደነበረም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን