
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወባማ ከኾኑ አካባቢዎች ውስጥ ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ከተመረመሩ 673 ሺህ 743 ሰዎች ውስጥ 127 ሺህ 647 የሚኾኑት በወባ በሽታ መጠቃታቸውን
የዞኑ ጤና መምሪያ የወባ እና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ኦፊሰር ወርቁ መንግሥቴ ነግረውናል።
በወባ ከተጠቁት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ደግሞ 10 በመቶ የሚኾኑት ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት፣ 2 በመቶ የሚኾኑት ደግሞ ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው።
በዚህ ዓመት በጸጥታው ችግር ምክንያት የተለያዩ ግብዓቶች መቆራረጥ እና ከዚህ በፊት በሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ላይ በባለሙያ ይሰጥ የነበረው ሕክምና በመቆሙ የወባ ሥርጭቱ ከዚህም በላይ ሊኾን እንደሚችል እና ቀድሞ መከላከል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ኦፊሰሩ እንደገለጹት የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል አሁን ላይ 25 ሺህ አጎበር ቀርቧል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 13 ሺህ በመተማ፣ 12 ሺህ የሚኾነው አጎበር ደግሞ በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው ቀበሌዎች እየተሠራጨ መኾኑን ገልጸዋል።
በምዕራብ አርማጭኾ እና አዳኝ ሀገር ጫቆ ወረዳዎችም የወባ ኬሚካል መመደቡን ገልጸውልናል። በቅርቡም ርጭት ይካሄዳል ብለዋል። ከዚህም ባለፈ አሁን ካጋጠመው የግብዓት እጥረት አኳያ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ዋነኛ የመከላከያ መንገድ ተደርጎ ቋሚ እና ጊዜያዊ የወባ መራቢያ ቦታዎችን በተደራጀ መንገድ የማፋሰስ እና የማዳፈን ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን