ዝክረ ሐምሌ አምስት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየታሰበ ነው።

36

ሁመራ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዝክረ ሐምሌ 05/2008 ዓ.ምን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየታሰበ ነው።

ዝክረ በዓሉን በማስመልከት የክልልና የዞን ከፍተኛ መሪዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የፓናል ውይይት እያደረጉ ሲኾን ዛሬ ደግሞ ከዞኑ ከተወጣጡ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በሁመራ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሐምሌ 05/2008 ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት የታወጀበት ነው ብለዋል። በአባቶቻችን፣ እናቶቻችን እና ወንድሞቻችን ትግል ነጻ ስለወጣን ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት።

ሐምሌ አምስት ሲታሰብ ጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሁሌ ይወሳል ያሉት ተሳታፊዎቹ በዚያች ዕለት እሱ በጀግንነት ባይጸና ዛሬ ያገኘነውን አማራዊ ማንነት ላናገኘው እንችል ነበር ብለዋል።

ይህ ቀን ነጻ የወጣንበት በመኾኑ በልኩ ልንዘክረው ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ የድልና የነጻነት ቀንን ማክበርና መዘከር ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠ ጸጋ መኾኑን አስረድተዋል።

ከጥንት አባቶቻችን የከፋኝ ትግል ጀምሮ “አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን የሚል ጥያቄ አንስተን አናውቅም” ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።

ጥያቂያችን የህልውና እንጂ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አይደለም፤ ለዚህም ነው ጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለሕዝባችን ጥያቄ እስከ ሞት ድረስ የታመነው ብለዋል።

ሐምሌ አምስት እንኳን ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለኢትዮጵያም የለውጥ ቀንዲል አድርገን ልንዘክረው ይገባል ነው ያሉት።

በመኾኑም ይሄ ትውልድ የትናንት ታሪኩን በወጉ በመረዳት ዛሬ ላይ የአባቶቹን አደራ በቁርጠኝነት በመረከብ የነገ ኀላፊነቱን በትጋት ለማከናዎን ሁሌም ዝግጁ እንዲኾን አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አሥተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ጥላሁን መኳንንት ሐምሌ አምስትን የምንዘክረው የእልፍ ጀግኖች ተጋድሎ ነፍስ የዘራበት ቀን ስለኾነ ነው ብለዋል።

የተገኘውን የነጻነት ድል በልኩ በመገንዘብ ቀኑን በታላቅ ተነሳሽነት ለመዘከር ዝግጁ መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ250 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወስደዋል።
Next articleወባን ለመከላከል ለአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ትኩረት መሥጠቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ገለጸ።