
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ እና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርን ለማስቀጠል መስማማታቸውን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሩ ስለሽ በቀለ (ዶክተር ኢንጂነር) እና ልዑካቸው ዛሬ ከሱዳን አቻቸው ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ሞሐመድ እና ልዑካቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተወያይተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ልዑካን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የሦስትዮሽ ድርድር ማስቀጠል በሚቻልባቸው ሀሳቦች ላይ ነው የተወያዩት፡፡
ልዑካኑ የሦስትዮሽ ድርድሩ እንደገና ስለሚጀምርበት፤ ድርድሩ ስለሚከናወንባቸው የስነ ስርዓት ጉዳዮች እና በግድቡ ላይ የሀገራቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተ መምከራቸው ተገልጧል፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች የሁለትዮሽ ስብሰባዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የሦስትዮሽ ስብሰባው በቶሎ እንዲጀመር ለማመቻቸት መስማማታቸው ታውቋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ከድርድሩ ጋር የተያያዙ ያልተፈቱ ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተም እንደተወያዩ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
