ከ250 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወስደዋል።

13

እንጅባራ: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መሬት መምሪያ የ2017 በጀት አመት የሥራ አፈፃፀሙን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሬት መምሪያ ኀላፊ በላይነህ የኔሰው የመሬት አሥተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ250 ሺህ በላይ የሚኾኑ አርሶ አደሮች በዘመናዊ የመሬት ልኬታ የታገዘ ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓልም ብለዋል።

የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት እየዘመነ በመምጣቱም በወሰን እና በይዞታ ይገባኛል ሰበብ የሚነሱ አለመግባባቶች እንዲቀንሱ፣ መንግሥት ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ እንዲሰበስብ እና የፍትሕ ተቋማት ተዓማኒ መረጃ እንዲያገኙ አስችሏል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ከ800 ሄክታር በላይ ያለአግባብ የተወረረ የወል መሬት እንዲመለስ መደረጉንም ገልጸዋል።

የግምገማው ተሳታፊዎችም መሬት የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመኾኑ በአያያዝና አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሂደት እየፈቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለዋስትና እንዲጠቀሙበት እና ሃብት እንዲያፈሩበት እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያም የተሻለ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓትን እውን ለማድረግ በ”ካልም” ፕሮጀክት ድጋፍ የተደረጉ 13 ሞተር ሳይክሎች ለወረዳዎች ተከፋፍለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሠራ ነው።
Next articleዝክረ ሐምሌ አምስት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየታሰበ ነው።