በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሠራ ነው።

9

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወባ ወረርሽኝ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለወባ ተጋላጭ መኾናቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና የበሽታዎች ቁጥጥር የሥራ ሂደት አስተባባሪ ዑመር የሻው በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የወባ ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ስምንት ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ ሕሙማን ሪፖርት የሚደረጉባቸው መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በዞኑ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በተመረጡ ወረዳዎች የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚኾን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለዚህም 115 ሺህ ከረጢት የጸረ ወባ ኬሚካል ተዘጋጅቶ ወደ ወረዳዎች መሰራጨቱን አንስተዋል።

እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ የኬሚካል ርጭቱን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ስለመኾኑም አመላክተዋል። ስርጭቱን ለሚያስተባብሩ ባለሙያዎች እና ለሚረጩ ሠራተኞች ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾኑን ጠቁመዋል።

ወባን ለመከላከል የአልጋ አጎበርም ለወረዳዎች እየተሰራጨ መኾኑን ነው የተናገሩት። በየሳምንቱ የወባ ክስተት ሪፖርት እየተቀበልን ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል።

የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ደረጀ ጎቤ በወረዳው የሚገኙ 23 ቀበሌዎች የወባ ወረርሽኝ ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከክረምት መግባቱ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በ15ቱ ቀበሌዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ማጨድ፣ ማፋሰስ እና ማዳከም የሚባሉትን የአካባቢ ቁጥጥር ሥራዎች እየሠራን ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

የጣቁሳ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኾነለት አየነው በበኩላቸው በወረዳው 31 ቀበሌዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው ኹሉም ቀበሌዎች የወባ ተጋላጭ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የወባ መራቢያ ሥፍራዎችን በመለየት የማጽዳት፣ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመለየት ሥራ፣ የአካባቢ ቁጥጥር፣ የጤና ትምህርት እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል ለወረዳው የተመደበ 94 ሺህ የአልጋ አጎበር ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም አመላክተዋል።

ማኅበረሰቡ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ውኃ የሚያቁሩ አካባቢዎችን እንዲቆጣጠር እና እንዲያጸዳ፣ የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ እንዲጠቀም፣ የሕመሙ ምልክቶች የታየበት ሰው ደግሞ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወባ ስርጭት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ አሳይቷል።
Next articleከ250 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወስደዋል።