
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ 12 ሺህ 291 የሚኾኑ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና መከላከልና መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ በላይሁን ከበደ ተናግረዋል፡፡
ይህ በ2016 ዓ.ም ከነበረው የወባ በሽታ ስርጭት ጋር ሲነጻጸር 33 በመቶ የሚኾን ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተለይም እንደ እንሳሮ፣ ምንጃር፣ መርሃቤቴ፣ ሸዋሮቢት እና መሰል ቆላማ የዞኑ አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ የኾነባቸው ናቸው፡፡
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ከወረዳ ባለሙያ እስከ ጤና ኤክስቴንሽን ድረስ የድግግሞሽ ሥልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
በየጤና ተቋማቱ የጤና ትምህርት በድግግሞሽ ወደ 2 ሚሊዮን ለሚጠጋ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወባ ስርጭት እንዳይስፋፋ እውቅና የመፍጠር ሥራ መሠራቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የወባ መራቢያ ይኾናሉ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን ውኃ ያቆሩትን የማፋሰስ፣ የማጨድ፣ የማዳፈን እና ውኃ የተጠራቀመባቸውን ቦታዎች ላይ ኬሚካሎችን የመበጥበት ሥራዎችም ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ መለስ የአጎበር አጠቃቀማቸውን ቤት ለቤት በመሄድ ክትትል ተደርጓል፡፡ በዚህም አጎበር ካላቸው 84 በመቶ የሚኾኑት በአግባቡ ተጠቃሚ መኾናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ወባን ለማጥፋት የአርብ እጆች መር በሚባል የጤና ክላስተር በየሳምንቱ ከፍተኛ የኾነ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አስተባባሪው በዚህም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
አስፈላጊ ግብዓቶችንም በማቅረብ በሽታውን ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ:- ሠናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን