
ደብረብርሃን፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከአጋር የጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመኾን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለሰላም አስከባሪ አባላት የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የምሥጋና እና ዕውቅና መርሐግብር አከናውኗል።
የሰላም አስከባሪ አባላቱ ከአጋር የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የከተማዋን ሰላም ለማስከበር በንቃት ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የሰላም አስከባሪ አባላቱ በቀጣይም የከተማዋን ሰላም ለማጽናት ሌት ተቀን እንሠራለን ብለዋል። የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ሁሉ ለመድረስ ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማው የሕግ የበላይነት እንዲከበር ያበረከታችሁት አስተዋጽኦ አኩሪ ተግባር ነው ብለዋል።
ከተማዋ የጀመረችውን የልማት እና መልካም አሥተዳደር የማረጋገጥ ሥራ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጥሩ እንቅስቃሴ እንዲገኝ የሰላም አስከባሪዎች ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ
በሚያደርጉ ፀረ ሰላም ኀይሎች ላይ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ለተወጡ ሰላም አስከባሪዎች በሙሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም አስከባሪ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ ከተማ አሥተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!