አረንጓዴው እሳቤ ከውስጥ ወደ ውጭ።

31

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቃዊቷ ኮከብ ኢትዮጵያ ጥቁር ለኾነ ሁሉ ማብራት የጀመረችው ዛሬ አይደለም። በዚያ በጨለማው ዘመን ለብዙዎች መመኪያ እና ኩራት ነበረች።

ኮርታ ማኩራት የቻለች ድንቅ ሀገርም ናት። ያቺ ታላቅ ሀገር ለአፍሪካውያን ጥላ ሁና መሠባሠቢያ በመመስረትም ትታወቃለች። ከኩዋሜ ኑክሩማ እስከ ሚምቤኪ እና ማንዴላ ድረስ እንደቤታቸው የሚያዩአት ደግሞም ጥላ ሁና ያላሳፈረቻቸው ሀገር ስለኾነች ነው። ይች ድንቅ ሀገር በየዘመናቱ በድንቅ ልጆቿ ሀሳብ ከራሷ አልፋ አህጉሩን የሚያኮራ ሥራ ስትሠራ ቆይታለች።

አሁን ደግሞ ዘመኑ የዚህ ዘመን ልጆች ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ ሀሳብ እና ትልቅ እሳቤ ያላቸው ፣ የማይነጥፍባቸው ልጆች እንዳሏት በዚህ ዘመንም አሳይታለች።

ለዓለም የራስ ምታት ለኾነው የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ትኾን ዘንድ አረንጓዴ ምድር የመፍጠርን ጽንሰ ሀሳብ እንካችሁ ብላ አስተዋውቃለች።

የዚህ እሳቤ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ከራሷ በመጀመር ጎረቤቶቿን በአረንጓዴ አሻራ አስተሳስራ ዓለምን ለመለወጥ ውጥን ሀሳብ ስታራምድ ብዙዎቹ በአግራሞት ተመልክተዋታል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ በ2011 ዓ.ም ክረምት ወቅት መባቻ ነበር የተጀመረው። ይኸው ድንቅ ሥራ ሲጀመር አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ በድምሩ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተቀምጦም ነበር።

ሥራው ከዕቅድ በላይም ተሳክቷል። ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሻገረ። በቀን 354 ሚሊየን ገዳማ ችግኞች ተተከሉ። በዚህ ዙር 20 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን ያኖሩበት ትልቅ ክስተትም ኾነ።

በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2012 ዓ.ም 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል። በተለይ የፍራፍሬ ተክሎች ላይም ትኩረት ተሰጥቶት ነበር።

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ተመራማሪው እና በዚሁ ቀጣና ምርምር የሠሩት ተስፋየ መብራቴ (ዶ.ር) እንደሚሉት ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ ተተግብሯል።

ይህ ዙር ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ አርዓያ እንድትኾን በማስቻል ለየት ያለ ባሕሪ ነበረው ይላሉ።

ተግባሩም ድንበር ዘለል ነበር። ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን መለገሷ ቅቡልነትን አስገኝቶላታል፤ ደንን በማልማት ጤናማ አካባቢ በመፍጠር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረንን ሰላም ለማረጋገጥም ያግዛል ባይ ናቸው።

ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተጀመረው ሦስተኛ ዙር መርሐ ግብር 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ተከናውኗል።

አራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር “አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሀሳብ 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ነበር። ሰኔ 14/2014 ዓ.ም በይፋ በተጀመረው በዚህ መርሐ ግብር ከዕቅድ በላይ መሳካትም ተችሏል።

ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መሪ ሀሳብ ‘ነገን ዛሬ እንትከል’ በሚል ተጀመረ። 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ላይ ያተኮረም ነበር። በ2015 ዓ.ም ክረምት ላይ የጀመረው ይህ ሥራ እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም የዘለቀም ነበር።

ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን ገጽታ መለወጥ፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የአቮካዶ አምራች ሀገር ማድረግ መሻት ያላት ሲሆን ለስኬታማነቱም ጥራት ያለው ፖሊሲ ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። ያለ ልዩነት ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት መረባረብ የግድ ይላል ባይ ናቸው።

በ2016 ዓ.ም ክረምት ላይ ለስድስተኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ615 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከልም ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እስካሁን ድረስ 40 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች፡፡

በዘንድሮ ዓመትም ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል አቅዳለች፡፡ ከነዚህም መካከል 50 በመቶ የሚኾነው ለምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ለውበትና ለአከባቢ ጥበቃ የሚውሉ ናቸው፡፡

ተመራማሪው እንደሚሉት ኢትዮጵያ እንዲህ አይነቱን ለትውልድ የሚሻገር ሥራ ሥትሠራ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ እንዳይኾን ቀድማ በማሰብ ጎረቤት ሀገሮችን እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን በዚሁ ተግባር አስተሳስሮ ለመልማት እያደረገችው ያለው ጥረት ብልህ መኾኗን ያሳያል ይላሉ።

የላይኛው ለምቶ የታችኛው ካለማ ዞሮ ዞሮ ከታችኛው ሀገራት ፍልሰት እና ችግሮች መኖራቸው አይቀሬ ነው ያሉት ተመራማሪው በጋራ መልማት የግድ ይላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ለዚህ ሥራ የማስተባበሩን ተግባር በሚገባ እየተወጣች እንደኾነ የሚያምኑት ተመራማሪው አሁን ላይ ዓለም በሥራው ቀልቡን እንዲሰጥ አድርጓል ባይ ናቸው።

ተመራማሪው አንድ ነገር ይመክራሉ፤ ይህ ሁሉ ልፋት እንዲሳካ ለተከላ የታየው የጋራ ርብርብ በተመሳሳይ ወደ ታኅሳስ አካባቢ ችግኞችን የመንከባከብ አጀንዳ ተቀርጾ መተግበር አለበት፤ በዚህም የፓለቲካ መሪዎች ተዋናይ ኾነው ማስተባበር አለባቸው። ሁሉም ለችግኞች መጽደቅ ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰላም ግንባታ ሂደቱ ላይ ሁሉም ባለቤት ኾኖ እንዲሠራ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
Next articleየሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ሁሉ ለመድረስ ዝግጁ መኾናቸውን የሰላም አስከባሪ አባላት ገለጹ።