
ባሕርዳር፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በክልሉ የሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጅ ዕቅድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) እንደገለጹት ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ከሕግ ማስከበር ባለፈ የሰላም አማራጭ ተዘርግቶ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም በርካታ የታጠቀ ቡድን በሰላም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀል ተደርጓል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከምሁራን፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ሰላምን ከሚሰብኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት እየተሠራም ይገኛል።
የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ሁሉም ዜጎች በሰላም ግንባታ ሂደቱ ላይ ሊሳተፉ ይገባል ነው ያሉት።
አለመግባባቶችን በውይይት እና በምክክር መፍታት ባሕል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) የአምስት ዓመት ሥትራቴጅክ ዕቅድን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ገዥ ኾኖ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በተፈጠረ የሐሰት ትርክት ክልሉ በሁለንተናዊ መልኩ የጥቃት ሰለባ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ጥቃቱ ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ኾኖ መቀጠሉንም አንስተዋል።
በ2021 ዓ.ም አስተማማኝ ሰላም እና የሕግ የበላይነት የሠፈነበት፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ተምሳሌት የኾነ ክልል ለመፍጠር በአምስት ዓመቱ ስትራቴጅክ ዕቅድ ትኩረት ተሠጥቶታል።
በስትራቴጅክ ዕቅዱ የተቋም እና የመሪ ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሁለንተናዊ ዘላቂ ሰላም፣ የድኅረ ግጭት አሥተዳደር መገንባት እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይዎት መመለስ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።
ብዝኀነትን ማሥተዳደር፣ የመልካም አሥተዳደር ግንባታ፣ አብሮነት፣ መልካም ግንኙነት፣ የባሕል እና ሰላም እሴት ተቋማትን ማጠናከር እንዲሁም ሌሎች ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ኾነው ተቀምጠዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን