
ፍኖተሰላም፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ጋር በመተባበር በከተማው ከሚገኙ የሴት ነጋዴዎች፣ አደረጃጀቶች እና መሪዎች ጋር በሰላም እና ልማት ጉዳይ ላይ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ስለእናት ዘሪሁን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሰላምን ለማጽናት የሕይወት መሰዋዕትነት እየተከፈለ መኾኑንም ተናግረዋል። ሴቶች ያላቸውን ሚና በመጠቀም ለሰላም ግንባታው የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።
ከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን በክረምት ወቅት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
የሰላም እጦቱ በቀዳሚነት በትሩን ያሳረፈባቸው ሴቶች መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን ናቸው። ካለው ግጭት ለመውጣት እና የተገኘው ሰላም እንዲጸና ሴቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
ሴቶች በዕውቀት፣ በጥበብ እና በአስተውሎት የተሞሉ እንዲኾኑ በማድረግ የልማት ሥራዎች ላይም ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለከተማው ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ነው ያሳሰቡት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ነጋዴው ነግዶ ያፈራውን ሃብት መጠቀም የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመኾኑ አሁን ያለው ሰላም እንዲጸና የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሰላም እና ልማት በአንድ አካል ብቻ የሚመጣ ባለመኾኑ ሴቶችም ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
መንግሥት ሴቶች በሚያደርጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ትምህርት በመቋረጡ በርካታ ሴቶች ለጋብቻ እና የፆታዊ ጥቃት ሰለባ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ነፍሰጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሂደው ለመውድ እየተቸገሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ሴቶች ለግጭት የመጀመሪያ ተጠቂዎች በመኾናቸው ለሰላም አምባሳደር ኾነው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
አሁንም ሰላምን አጥብቀን ስለምንሻ ለሰላም መስፈን በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
ከሰላም ግንባታው ጎን ለጎን ሴቶች የራሳቸውን ኢኮኖሚ በማሳደግ ለከተማው ልማት መፋጠን ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን