የአማራ ክልል የብልጽግና ጉዞ አብሳሪ ክልል ነው።

31

ጎንደር: ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ጠንካራ አደረጃጀት ለሁለንተናዊ ብልጽግና በሚል መሪ መልዕክት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 እቅድ ትውውቅ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። ‎

‎በመድረኩ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ፣ የ2018 እቅድ ትውውቅ እና የአረንጓዴ አሻራ እቅድ እንደሚቀርብ ተገልጿል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይም በዕለቱ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

‎የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍቃዱ ተሰማ በአደረጃጀቶች የተከናወኑ ሥራዎች ተስፋ ሰጭ መኾናቸውን አንስተው የአማራ ክልል የብልጽግናን ጉዞ አብሳሪ ክልል ነው ብለዋል።

‎የአማራ ክልል የብልጽግና እሳቤ ያለው፣ የሀሳብ እና የተግባር አንድነት ያለው፣ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ሥራዎችን አጣምሮ እየሠራ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል። ‎በጀት ዓመቱ ድሎች እና ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል።

‎ዓመቱ ከቃል እስከ ባሕል በሚል መሪ መልዕክት ጉባኤ የተካሄደበት፣ ትርጉም ያለው ሥራ የተሠራበት፣ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል ጥረት የተደረገበት፣ የኮሪደር ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች እንዲኹም ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማስመረቅ ዋዜማ ላይ የተገኘንበት፣ ለሰላም መረጋገጥ የተሠራበት እና አንድነት የታየበት ጊዜ መኾኑን ገልጸዋል።

‎በሁሉም መስክ የኢትዮጵያውያንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተሠራበት ዓመት መኾኑንም ተናግረዋል። ‎የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት እና ሰላምን በሚፈለገው ልክ ማስፈን ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

‎የአደረጃጀት ግንዛቤ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ‎በመኾኑም መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር ችግሮችን ለመፍታት መትጋት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።

‎የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ችግር ገጥሞት የነበረ መኾኑን አንስተው ክልሉ ችግር በገጠመው ጊዜ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ረገድ የብልጽግና መሪዎች ሚና ከፍ ያለ መኾኑን ተናግረው ለዚህም አመስግነዋል።

‎ሰላም እንዲሰፍን፣ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ብሎም የብልጽግና ሁለንተናዊ ጉዞ እንዲረጋገጥ ፓርቲው እና የፓርቲው አባላት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እያበረከቱ በመኾኑ ኩራት ይሰማናል ብለዋል። ‎

ክልሉ በሁሉም ዘርፍ ልማት ላይ ያለ እና አንፃራዊ ሰላም ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።

‎ብልጽግና በችግር ውስጥም ኾኖ ትልልቅ የልማት ሥራዎችን እየሠራ እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ እያጠናቀቀ እንደሚገኝም አማራ ክልል ማሳያ ነውም ብለዋል።

‎የክልሉ ሕዝብ ልማት እና ሰላም ወዳድ መኾኑን ያነሱት አቶ ፍስሐ በሁሉም የክልሉ ክፍሎች የሰላም እና የልማት ፍላጎት በድጋፍ ሰልፍ የተረጋገጠበት በልማት ሥራዎችም ተሳትፎ የታየበት መኾኑን አመላክተዋል።

‎በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር ዛሬ በልማት ጎዳና ላይ ያለች ከተማ መኾኗን አንስተዋል። ትናንት ተረስታ የቆየች ከተማ ብትኾንም ዛሬ ላይ የበርካቶችን ትኩረት ስባለችም ብለዋል።

‎ልማቷ በዚህ ብቻ አያበቃም ያሉት ከንቲባው በቀጣይም ያሉ ምቹ ኹኔታዎችን ሁሉ ተጠቅመን እንደ ቀደመ ታሪኳ በጥበብ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በዘመናዊነት እናበለጽጋታለን ነው ያሉት። ‎

ብልጽግና ፓርቲ የልማት ሥራዎች ላይ ያለውን ሚና የምታሳይ ከተማ ናት ብለው ፓርቲውን ለሁለንተናዊ አበርክቶው አመስግነዋል።

‎ለጎንደር ልማት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የፌደራል፣ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች እና ለልማት አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ ምስጋናን አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ:- ‎ቃልኪዳን ኀይሌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሰላምን በዘላቂነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
Next articleበጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የነዋሪዎቹን የሥራ ባሕል መቀየር የቻሉ ናቸው።