
ሁመራ፡ ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል፣ የዞን ከፍተኛ መሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ በሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከናውኗል።
አረንጓዴ አሻራቸውን ያስቀመጡት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የዞኑ ሕዝብ እና መሪ በመቀናጀት ችግኝ ይተክላል በመናበብ የአካባቢውን ሰላም ያጸናል ነው ያሉት።
በሀገር፣ በክልል እና በዞን ደረጃ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጠላትን መመከት አማራነትን ማጽናት ብሎም ኢትዮጵያዊነትን ማላቅ የሚያስችል ትብብር እየታየበት መኾኑን አቶ አሸተ ደምለው አብራርተዋል።
ሰላምን በዘላቂነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የዛሬው ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የነጻነት ዝክረ ቀን በዓልን አስመልክቶ ከሚከናዎኑ ተግባራት መካከል መኾኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ተቋማት የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ረገድ ለሌሎች ተቋማት እና ለማኅበረሰቡ አርዓያ መኾን አለባቸው ያሉት ደግሞ የሁመራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ኢንጅነር ጠጁ መሰለ ናቸው።
እነዚህ ተቋማት መሪ ኾነው መገኘት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ይህ በመኾኑም በዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በኮሌጁ ችግኝ እየተተከለ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የሁመራ ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ ሰለሞን በላይ ትውልዱ ታላላቆቹ የሚያደርጉትን ነገር ስለሚከተል እኛም በጎ አሻራ በማሳረፍ ለትውልዱ ምሳሌ ለመኾን እየሠራን ነው ብለዋል።
የዞኑ ሕዝብ ከመሪዎቹ ጋር በመቀናጀት በልማት እና በሰላም ግንባታው ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መኾኑን አንስተው ይሄም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን