የወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው።

15

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት የወባ በሽታ እየጨመረ እንደመጣ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማን የተመዘገበ ሲኾን በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማን ተመዝግቧል።

በክልሉ የሚገኙ 40 ወረዳዎች የክልሉን 70 በመቶ የወባ ሥርጭት ይይዛሉ ተብሏል። በክልሉ ወባማ ከኾኑ አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ደቡብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። እስካኹን ከ412 ሺህ በላይ የወባ ሕሙማን ተመዝግበዋል።

በደራ ወረዳ አምበሳሜ አካባቢ ነዋሪ የኾነው አበባው አየነው ከዚህ በፊት የወባ ሕመም አጋጥሞት እንደማያውቅ ነገረን። ይኹን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው የወባ ሥርጭቱ በመጨመሩ የወባ ተጠቂ መኾኑን አንስቷል።

በአምበሳሜ ጤና ጣቢያ በርከት ያሉ በወባ የተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች መመልከቱንም ነግሮናል። ከዚህ በፊት ማኅበረሰቡ በአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንዲሠራ ቢደረግም ሥርጭቱ አኹንም የማኅበረሰብ ሥጋት መኾኑንም ነው የገለጹት።

የደራ ወረዳ አምበሳሜ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ጌታሰው አባተ አምበሳሜ ጤና ጣቢያው ጉድኝት ወባማ ከኾኑ አካባቢዎች አንዱ ነው።

በጤና ጣቢያው እስከ ሰኔ 20/2017 ዓ.ም የወባ ምርመራ ከተደረገላቸው 36 ሺህ 414 ሰዎች ውስጥ 15 ሺህ 177 ሰዎች ወባ ተገኝቶባቸዋል።

ሕጻናት እና ነፍሰጡር እናቶች ደግሞ ከተጠቁት የኅበረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ችግሩን ለመከላከል በ”አርብ እጆች” መርሐ ግብር የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ መቆየቱን ነው ያነሱት።

መርሐ ግብሩ የወባ ሥርጭቱን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ገልጸዋል።

የማኅበረሰቡን በራስ የመከላከል አቅም ያሳደገ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ሕሙማንም የማከም ሥራ የሚሠራ ይኾናል ብለዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ እጸገነት አምላክ በዞኑ
በ2017 በጀት ዓመት ከተመረመሩት
938 ሺህ 430 ሰዎች ውስጥ 412 ሺህ 995 ሰዎች በወባ መጠቃታቸውን ገልጸዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት በ48 ሺህ 585 ሰዎች ብልጫ አሳይቷል።

ከዚህ በፊት የወባ በሽታ ወቅትን መሠረት አድርጎ ይከሰት እንደነበር ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ አኹን ላይ ከዚያም ባለፈ ኹኔታ እየተባባሰ መኾኑን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ደራ፣ ፎገራ፣ ሊቦከምከም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወባ ሕሙማንን የሚያስተናግዱ ወረዳዎች መኾናቸውን ነው የገለጹት።

ሥርጭቱን ለመከላከል ከዚህ በፊት “በአርብ እጆች” መርሐ ግብር ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ የወባ መራቢያ አካባቢዎችን የማዳረቅ፣ የማፋሰስ ሥራ በቋሚነት ሲሠራ ቆይቷል።

በቀጣይም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራው እንደ ዋነኛ መፍትሔ ተደርጎ እንደሚሠራ ነው ያነሱት።

ዘጋቢ፡ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleማኅበረሰቡ የወባ በሽታን መከላከል ላይ እንዲያተኩር የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አሳሰበ፡፡
Next articleየሚመዘበር ንብረትን በመከላከል ለልማት ማዋል እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል።