የቆቦ ጊራና የሸለቆ ልማት የሕልም እንጀራነት እስከመቼ?

454

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቆቦ ጊራና የሸለቆ ልማት ጉዳይ ለአርሶ አደሮች ‘‘ላም አለኝ በሰማይ’’ እንደሆነባቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው ቆቦ ጊራና የሸለቆ ልማት ፕሮጀክት በ1991 ዓ.ም ተመሥርቶ በ1995 ዓ.ም የመስኖ ሥራ ጀምሯል፡፡ በሸለቆው ያለውን የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት በመጠቀም አርሶ አደሮችን ከድህነት ማውጣት፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ለመከወን ነበር የተጀመረው፡፡ በአስር ዓመታት ውስጥ ማለትም እስከ 2005 ድረስ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት እቅድ የመጀመሪያ ግቡ ነበር፡፡ ከራያ ቆቦ፣ ከሀብሩ እስከ ባቲ እና ሸዋሮቢት ስምጥ ሸለቆዎች ድረስ ያሉ አከባቢዎችን ያለማልም ተብሎ ነበር፡፡ አሁን በ2012 ዓ.ም ከ17 ዓመታት በኋላም ግን ፕሮጀክቱ 2 ሺህ 741 ሄክታር መሬት ብቻ ነው ማልማት የቻለው፡፡ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ግን ዛሬም ጾማቸውን አልፈቱም፡፡

ለምን?

የቆቦ ጊራና የሸለቆ ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ሞላ መለሰ ‘‘ችግሩ ፕሮጀክቱ ሲመሠረት የራሱ የኃይል ማከፋፈያ (ሰብስቴሽን) አለማሟላቱ ነው’’ ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ አሁን ባለው የኃይል አቅርቦት ከዚህ በላይ መስፋፋት እንደማይችል የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ‘‘የኃይል አቅርቦት እንዲኖር 38 ሚሊዮን ብር ለመስመር ዝርጋታ ቢከፈልም የኃይል ማከፋፈያ ሳይኖር ኃይል ማምጣት እንደማይቻል በመነገሩ ባለው አቅም ብቻ እንዲሠራ ተገድዷል’’ ብለዋል፡፡ ከጥልቅ ጉድጓዶች ውኃ የሚስቡ የ‘ፓምፕ’ እና ‘የፓናል ወርድ’ መሣሪያዎችን ማግኘት አለመቻልም የአርሶ አደሮችን ኑሮ መሻሻል ፈተና ሆነውበታል፡፡

ስምጥ ሸለቆን በጭልፋ

የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮጀክት በዚህ ወቅት 10 ሺህ አባወራና እማወራ ልማት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሸለቆ ልማቱ የ17 ዓመታት ጉዞ 269 ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 82 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ቢጠናቀቅም የሚሠሩት ግን 64 ብቻ ናቸው፡፡ በእነዚህ 64 ፕሮጀክቶች በዓመት ሦስት ጊዜ ምርት ይሰበሰባል፡፡ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ምርት ብቻ ከ2 ሺህ 741 ሄክታር መሬት 95 ሺህ 193 ኩንታል ሀብሀብ፣ ፓፓያ እና ሽንኩርት ተገኝቷል፡፡ ‘‘ከእቅዱ በላይ አሳክተናል’’ ያሉት አቶ ሞላ ከ284 ሚሊዮን 671 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

የሸለቆ ልማቱ በአዳዲስ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝሪያዎች ማላመድ እና ማሻሻል ሥራዎቹ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን የተናገሩት አቶ ሞላ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም ሥራ ቢጀምር ኑሮ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚኖረውን አርሶ አደሮች ሕይወት በአንድ ዓመት ጊዜ መቀየር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ዋና ትኩረት አድርገው ቢሠሩ ከሀገር ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ገበሬዎች

አቶ ሻምበል ሞላ የመንግሥት ሠራተኛ እና ነጋዴ ሆነው በቆቦ ከተማ ሠርተዋል፡፡ የቆቦ ጊራና የስምጥ ሸለቆ ፕሮጀክት የቤተሰቦቻቸውን ማሳ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በወቅቱ የግብርና ሥራ ሕይወታቸውን ይለውጣል ብለው ባለማሰባቸው በፕሮጀክቱ የቤተሰቦቻቸው ማሳ ጤፍና ሽንብራ በመዘራቱ ለውጡ ያን ያህል እንዳነበረ ያስታውሳሉ፡፡ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ባለመሰማራታቸውም ዓመታትን እንደዋዛ አሳልፈዋል፡፡ ከአራት ወራት በፊት ግን ሕይወታቸውን የሚቀይር ውሳኔ ወስነዋል፤ በዚህም ‘‘ያሳፍኩት ጊዜዬ ያሳዝነኛል’’ ይላሉ፡፡ አቶ ሻምበል 48 ሺህ ብር አውጥተው የገዙትን የቃሪያ ችግኝ በአንድ ሄክታር መሬት ውስጥ ዘተክለው በአራት ወራት ውስጥ ደርሶ ሦስት ጊዜ ምርት አፍሰዋል፤ ለሦስት ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በሦስት ዙር ብቻ 357 ሺህ ብር ማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ ሻምበል ከዚህ በኋላም እስከ ሰባት ጊዜ መልቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር መንገሻ አከለ ከ6 ዓመታት በላይ የዝናብ ውኃ በማሰባስብ የጀመሩት የመስኖ ልማት ሥራቸው በሸለቆ ልማት ፕሮጀክቱ ታግዞ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በአንድ ዓመት እስከ 50 ሺህ ብር ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‘‘ከሽንኩርት በተጨማሪ 40 ቋሚ የማንጎ ዛፎች አሉኝ’’ ያሉት አቶ መንገሻ እያንዳንዳቸው 250 ፍሬ በአማካኝ እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ‘‘አንድ ፍሬ ማንጎ እስከ 24 ብር እየሸጥን ነው’’ ያሉት አርሶ አደሩ ሁሉም የማንጎ ፍሬዎቻቸው ቢሸጡ እስከ 240 ሺህ ብር በዓመት ሊያገኙ እንደሚችሉም አመላክተዋል (ማንጎው በልማድ ከሚታወቁት ፍሬዎች የበለጠ ትልቅ ፍሬ ያለው ነው፡፡

መሶብ ሞልቶ ያስራበን ምንድን ነው?

ጓዳን የሚሞላ የከርሰ ምድር ውኃ እና ለም መሬት ቢኖርም የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፍለጋ ለሥደት ይዳረጋሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር በትኩረት ባለመሥራቱ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ነግረውናል፡፡ ፕሮጀክቱ ከቆቦ፣ ሀብሩ፣ ባቲ፣ አጣየ ድረስ የማልማት አቅም ቢኖረውም ባለፉት 17 ዓመታት 5 በመቶው አካባቢ ብቻ ነው መልማት የጀመረው፡፡

በቆቦና አካባቢው የሚኖሩ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ፕሮጀክት ታዲያ ለምን ከ19 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እንዲያለማ አልተሠራም?

የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይክተር አደም ወርቁ አካባቢው ሰፊ የከርሰ ምድር ውኃ እና ለአትክልትና ፍራፍሬ ምቹ ቀጣና እንደሆነ እንደሚታወቅ ገልጸዋል፡፡ የቀጣናውን ልማት እንዳይሰፋ ማነቆ የሆነው ራሱን የቻለ የኃይል ማከፋፈያ አለመኖር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የቀጣናውን አርሶ አደር ሕይወት በመቀየር የሀገሬቱን ገበያ ለማጥገብ የሚያስችል በመሆኑ ‘‘የኃይል ማከፋፈያ እንዲኖር ያልጠየቅንበት ጊዜ የለም’’ ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ የስምጥ ሸለቆ ልማት ከቆቦ እስከ ሰሜን ሸዋ የሚደርስ ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ትልቅ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሉ በየዓመቱ የፌዴራል መንግሥት እንዲያግዘው ከመጠየቅ ባለፈ መልስ አለማግኘቱን ነው አቶ አደም የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ደግሞ ከቆቦ እስከ ሰሜን ሸዋ የሚሄድ አንድ ሰብስቴሽን እንደማይኖርና ከአራት እስከ አምስት ሰብስቴሽኖች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ‘‘በዚህ ወቅት ራሱን ችሎ ሰብስቴሽን ይገነባል የሚል ዕቅድ የለም፤ እኔም አላውቀውም’’ ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ‘‘ከዚህ በፊት ጠይቀዋል አልጠየቁም?’’ ስለሚለውም ጉዳይም በሰፊው ማጣራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቁት፡፡ ነገር ግን የመስኖ ‘‘ፕሮጀክቱ በሚደርስባቸው አካባቢዎች ኃይል እንዲቀርብ የማድረግ ሥራ ተጠንቶ ሊሠራ ይገባል’’ ነው ያሉት፡፡ ፕሮጀክቱ በቁርጠኝነት የመስፋፋት መርሀ ግብር ካለው የወልዲያ እና የደሴ የኃይል ማከፋፈያ ጣብያዎችን አቅም በመጠቀም በሚደርስበት ሁሉ ኃይል እንዲያገኝ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ውስጥ የቡና ኤግዚቢሽን አካሄደች፡፡
Next articleተጨማሪ 87 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡