የሚመዘበር ንብረትን በመከላከል ለልማት ማዋል እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል።

13

ጎንደር: ሐምሌ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በፌደራል እና በክልሉ በቅርቡ የፀደቁ ሦሥት አዋጆች ላይ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ለምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ለሰሜን ጎንደር ዞን እና ለጎንደር ከተማ አሥተዳደር ዳኞች እና ዐቃቢያን ሕጎች በጎንደር ከተማ ሥልጠና ሰጥቷል። አዋጆቹ የንብረት ማስመለስ፣ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ የተመለከቱ ናቸው።

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ የንብረት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ልየው ፀሐይ የወጡ አዋጆችን በተደራጀ መልኩ ለመፈፀም ለባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የንብረት መዝረፍ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ምጣኔ ሃብቱ እንዳይረጋጋ እና የሀገር ሰላምን ስለሚያውክ ዳኞች እና ዐቃቢያነ ሕጎች አዋጁን አውቀው መከላከል ይገባቸዋል ብለዋል። ተገቢ ባልኾነ መንገድ ጥቅምን ማሣደድ የሕዝብን የልማት ፍላጎት እንደሚያሳጣም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ፍትሕ ቢሮ የሕግ ምክር ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ መስፍን መኮንን አዳዲስ የወጡ ሕጎችን በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ሕገ ወጥነትን መከላከል እና መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ለሚጠበቀው ሥራ መሣካት እና ፍትሕን ለማረጋገጥ በአዋጆቹ ላይ መረዳት እና ወጥነትን ማረጋገጥ ይጠበቃል ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ አየልኝ ደሳለኝ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚገኝን ንብረት እና ጥቅም ማሣጣት ያልተገቡ ድርጊቶችን ለመከላከል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ሥልጠናው የምጣኔ ሃብት ወንጀሎችን ለመከላከል ወቅቱን የጠበቀ እንደኾነ አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው።
Next articleበኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተሠሩ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ።