
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወባ በሽታ በተደጋጋሚ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው፡፡
በጃዊ ወረዳ የፈንዲቃ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሙሉየ ውበት በወባ በሽታ ኅብረተሰቡ እንደሚቸገር ይናገራሉ፡፡ ችግሩን ለመቋቋምም የጤና ባለሙዎችን ምክር እንደሚተገብሩ ገልጸዋል፡፡
ጎረቤቶቻቸውን በማስተባበር የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ እና አጎበር በመጠቀም ወባን እንደሚከላከሉ ነው ወይዘሮ ሙሉየ የተናገሩት፡፡ በወባ በሽታም ታምመው አያውቁም፡፡
ሰሞኑን የወባ ክስተቱ መበራከቱን ወይዘሮ ሙሉየ ጠቁመዋል፡፡
በጃዊ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ወሰን ትዕዛዙ ወረዳው ለወባ ተጋላጭ መኾኑን ጠቅሰው የመከላከል ሥራም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ማኅበረሰብ ራሱን ከወባ እንዲከላከል ግንዛቤ መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡
ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የወባ ሕሙማን ቁጥር ቢጨምርም የወባ በሽታው በወረዳው በወረርሽኝ ደረጃ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህ ዘገባ ከመጠናቀሩ አራት ሳምንታት ቀደም ብሎ በወረዳው የወባ ታማሚዎች ቁጥር ጭማሪ እንዳላሳየ ተናግረዋል።
የየደረጃው ባለሙያዎች በንቃት እያገለገሉ መኾኑን አንስተው ፕሩማኩይን እና ክሎሮኪን የሚባሉ መድኃኒቶች እጥረት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ እነዚህን መድኃኒቶች እና የአጎበር አቅርቦትም መጠየቃቸውን ነው አቶ ወሰን የገለጹት፡፡
ሕዝቡን በማስተባበር እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን በመጠቀምም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ወሰን አስገንዝበዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አየለ አልማው 72 በመቶ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ በወባ ተጠቂ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አምስት ወረዳዎች እና አንድ ከተማ አሥተዳደር ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ መኾናቸውን እና ከዞኑ የወባ ሽፋን 84 በመቶ እንደሚይዙ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አየለ በግንቦት የተከሰተው የወባ በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ እንደነበር ገልጸው በሣምንት እስከ 11 ሺህ የወባ ታማሚ በጤና ተቋማት መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ በነበረው የወባ መከሰቻ ጊዜ ከፍተኛ ሥራ ሠርተናል ያሉት አቶ አየለ ባለሙያዎችን አሠልጥኖ በማሠራት ወባ ያደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጉዳት መቀነስ ችለናል ብለዋል፡፡
የግንዛቤ ፈጠራ፣ የአካባቢ ቁጥጥር፣ የአጎበር መጠቀም፣ የኬሚካል ርጭት እና በወባ ከተያዙም በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም ሂዶ የመታከምን ሥራዎች በቅድመ ዝግጅት እና በትግበራ ላይ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ከአምሥት ዓመት በፊት የተሰራጨው አጎበር በማርጀቱ ከክልል ጋር በመነጋገር ለማቅረብ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ሦስት ወረዳዎችም አጎበር ማግኘታቸውን እና በቀጣይም የሚቀርብላቸው ወረዳዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በሁለት ወረዳዎች በ30 ቀበሌዎች የቤት ውስጥ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ በጀት እና ኬሚካል መፈቀዱን ያነሱት ኀላፊው በቅርቡ ርጭቱ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
ከመከላከል ሥራው አልፎ ለሚታመሙ ሰዎች ደግሞ ህክምና ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን አንስተው ለወረዳዎች ከሚደረገው ድጋፍ ውስጥ ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ ድጋፉን በማቋረጡ ምክንያት እጥረት መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የክልሉን ጤና ቢሮ ድጋፍ እየጠየቁ መኾኑን አንስተዋል፡፡
መድኃኒት ውጭ ግዙ ስለመባሉ ለተነሳላቸው ጥያቄም የወባ ሕክምና የሚሰጠው በነጻ ስለኾነ ችግሩ እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡
ማኅበረሰቡ ወባን ለመከላከል ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያነሱት አቶ አየለ የትንኝ መራቢያን ማጽዳት፣ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም፣ ኬሚካል የተረጨውን ቦታ አለመለቅለቅ እና አለመለጠፍ እንዲሁም የወባ ምልክት የታየባቸው እና የታመሙትን ወደ ጤና ተቋም ወስዶ ማሳከም እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን