አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 5/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በሚቀርቡ አጀንዳዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በምክክሩ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮምሽን ምክትል ዳይሬክተር ሀናን ሙርሲ ኢትዮጵያ ይሄን ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማዘጋጀት መፍቀዷ ምሥጋና እና ዕውቅና ይገባታል ብለዋል።
ሀገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ፖሊሲ ነድፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረጓም የሚደነቅ እና በውጤት የታገዘ ነው ብለዋል።
በተለይ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዋ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከሏ የዚህ አካል እንደኾነ ነው ያስረዱት።
አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ተምረው ደግሞም ተቀናጅተው በመሥራት የአየር ንብረት ለውጥን መታገል እና ዘላቂ ኢኮኖሚን መገንባት ይገባቸዋልም ብለዋል።
የኢፌዲሪ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር) ጉባኤው ወሳኝ አጀንዳዎች ተመርጠው ውጤታማ ምክክር የሚደረግበት እንደሚኾን ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ፎረም በመንግሥት እና በልማት አጋሮች መካከል የአየር ንብረት ተፅዕኖዎች ላይ የሚወሰዱ ርምጃዎችን በማስተባበር ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን አመራር የምታሳየው እንደ አረንጓዴ ሌጋሲ ተነሳሽነት፣ ታዳሽ ኀይል ምርት፣ የዘመነ ግብርና፣ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት፣ ጽኑ ፖሊሲዎች እና ለውጥ አምጭ የአየር ንብረት-ስማርት መሠረተ ልማት ባሉ ጠንካራ ሀገራዊ ተግባራት ነው ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጎላ ሚና ባይኖራትም ዳፋው ግን በብዙ እየጎዳት ነው ያሉት ዶክተር ፍፁም በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉና ዕድገታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ለአፍሪካ የቴክኖሎጅ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ማገዝ ይገባቸዋል ብለዋል።
ጉባኤውም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት።
በምክክር መድረኩ ሌሎች አጀንዳ መኾን ያለባቸው ሀሳቦችም በተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን