የጠለምት ተፈናቃዮች በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አሳሰበ።

10

ባሕር ዳር፡ሐምሌ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ የአብና ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሞላ ኃይሌ በ2016/17 የክረምት ዘመን በደረሰው የመሬት ናዳ ከቤታቸው ተፈናቅለው ከሰባት ቤተሰቦቻቸው ጋር በመጠለያ ውስጥ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ከክረምት ቁር እና ከበጋ ሀሩር አልተላቀቁም፡፡

ችግር ላይ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ ሞላ መንግሥት ከችግራቸው በዘላቂነት የሚወጡበትን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአደጋ መከላከል እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ መሠረት ጥላሁን በነሐሴ 2016 ዓ.ም በስድሰት ቀበሌዎች ላይ የተፈጥሮ አደጋ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በአብና ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የሰዎች ሕይዎት ማለፉን እና 2 ሺህ 400 ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡

እስካሁን ድረስ 150 አባዎራዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን፣ 160 አባዎራዎች ከነቤተሰባቸው በመጠለያ ቦታዎች መኾናቸውን እና ቀሪዎቹ ደግሞ በዘመድ አዝማድ መጠለላቸውን ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በገበሬ ማሠልጠኛ እና መሰል ቦታዎች ላይ መጠለላቸውን የገለጹት አቶ መሠረት በዘላቂነት ማስፈሪያ ቦታ መጥፋቱንም ነው የተናገሩት፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናትም ተፈናቃዮቹን ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለስ አደጋ እንደሚኖረው ማመላከቱን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው መንግሥታዊ ባልኾነ ድርጅት እና በሌሎች ወገኖች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት አቶ መሠረት አሁን ግን ምንም ዓይነት መጠባበቂያ እህልም ኾነ ቁሳቁስ አለመኖሩን አንስተዋል፡፡ ስለኾነም ምግብ እና ሌሎች የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ሊኖር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የጠለምት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ጋሻው እንግዳው ለተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብ፣ የአልባሳት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የከፋ ችግር ያለባቸው እና ቅድሚያ የሚሹት 23 አባዎራዎች መኾናቸውን ገልጸው ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በቀበሌው መሥፈሪያ ቦታ መጥፋቱንም ጠቅሰዋል። በጎረቤት ቀበሌዎች ለማስፈርም የተቋቋመው የጥናት ኮሚቴ መዘግየቱን ነው የተናገሩት።

አቶ ጋሻው ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ ከዞን አሥተዳደር እና ከክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ጋር ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

በአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በአደጋው ለተፈናቀሉ ሰዎች በበጋው ወራት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ለዘላቂ መፍትሄው ኀላፊነቱ የቀበሌ እና የወረዳ አሥተዳደሩ መኾኑን አንስተዋል።

ተፈናቃዮቹ እስካሁን በመጠለያ ውስጥ መኾናቸው ተገቢ አለመኾኑን እና በወረዳ ደረጃ ቦታ ተፈልጎ የአደጋ ቦታውን እንዲለቅቁ መደረግ እንደነበረበት ነው የገለጹት፡፡

በቀበሌው ውስጥ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ተፈናቃይ ናቸው ማለት እንደማይቻል የገለጹት አቶ ብርሃኑ መሬታቸው፣ እንስሳቶቻቸው እና አጠቃላይ ኑሯቸው የተመሠረተው እዚያው ቀበሌ ላይ በመኾኑ ከቀበሌያቸው ላይ መስፈሪያ እና ቤት መሥሪያ ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው አሥተዳደር ተፈናቃዮቹን በአስተማማኝ ቦታ ለማስፈር በሚያደርገው ጥረት ከአቅሙ በላይ የኾነ ችግር ካጋጠመው ድጋፍ መጠየቅ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮም የክረምቱ ዝናብ ከባድ እንደሚኾን ትንበያ በመኖሩ የመሬት ናዳ ተጋላጮችን ቀድሞ ከአደጋው ማራቅ እንደሚገባም ነው አቶ ብርሃኑ የመከሩት፡፡

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የአቅመ ደካሞችን እና ቤት በመጠገን እና በአዲስ በመሥራት የዜጎችን ሕይዎት የመታደግ ሥራ እየተሠራ ነው።
Next articleኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ፖሊሲ ነድፋ ተግባራዊ ማድረጓ የሚደነቅ ነው።