
ፍኖተሰላም፡ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ የአቅመ ደካሞችን እና የተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቤት በመጠገን እና በአዲስ በመሥራት የዜጎችን ሕይዎት የመታደግ ሥራ እየተሠራ ነው። ”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በምዕራብ ጎጃም ዞን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ በክረምት ወቅት በልዩ ትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካማ ቤት እድሳት አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።
የአቅመ ደካሞችን እና የተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቤት በመጠገን እና በአዲስ በመሥራት የዜጎችን ሕይዎት የመታደግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
በዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በርብርብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለያዩ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች 548 ሺህ 218 በላይ የኅብተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሥራውን ለማከናወን እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ በዕውቀቱ ተሾመ ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ ሥራው 118 የአቅመ ደካማ ቤቶች በአዲስ የሚሠሩ ሲኾን 235 ቤቶች ደግሞ እድሳት የሚደረግላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
የሚከናወነው የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማስቀረት የሚችል መኾኑም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።