
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ውስጥ ለተለያዩ ሀገራት የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት ዛሬ የቡና ኤግዚቢሽን ቅርባለች፡፡
አዘጋጁ በእስራኤል የኢትየዮጵያ ኤምባሲ ነው፡፡ ዝግጅቱን ለማካሄድ ምክንያት የሆነው ደግሞ በእስራኤል ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ስለኢትዮጵያ ቡና የሚያውቁት ሰዎች ጥቂት መሆናቸውን በማረጋገጡ መሆኑን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
በዝግጅቱ የቡና አፈላል ሂደቶች ለታዳሚያኑ ቀርበዋል፤ ሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ መለያ ከሆኑ ውብ ባህሎች አንዱ ስለመሆኑም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ሀገሪቱ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ልዩ ጣዕም ያለውና የተመራጭ ቡና ባለቤት መሆኗንም በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስገንዝቧል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ በሚፈለገው ልክ አለመግባቱን ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡፡ ለእስራኤል ምርቱን ለማጓጓዝም የምትቀርባት ኢትዮጵያ ሆና እያለ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላቲን አሜሪካ ሀገራት ማምጣቷ በአብነት ተጠቅሷል፡፡ በሀገሪቱ የኢትዮጵያን ቡና የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች መሆናቸውም ሌላ ማሳያ እንደሆነ ነው ኤምባሲው ያሳወቀው፡፡
በመሆኑም አሁን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚመጣውን የቡና መጠን ማሳደግ እንደሚገባ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ለማሻሻልም ኤምባሲው ከቡና አስመጪዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓቱን እስራኤል ውስጥ በሚገኙ ከ25 በላይ የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶች ማስለመድ እንደሚገባም ሐሳብ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር 2020 (እ.አ.አ) ቴላቪቭ ውስጥ የቡና ኤግዚቢሽን ማቅረቧ ይታወሳል፡፡
ዛሬ በተካሄደው ዝግጅት ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ባለቤቶች፣ የአፍሪካ ሀገራት እና የእስራኤል የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት መሳተፋቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአስማማው በቀለ
ፎቶ፡- ወንድይፍራው መንግሥቴ -ከእስራኤል
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
