“በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች መድረስ መንግሥታዊ ብቻ ሳይኾን ሞራላዊ ግዴታም ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

30

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በባሕርዳር ከተማ አሥጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በጎነት ለራስ ነው፣ በጎነት ለአማራ ክልል ሕዝብ ባሕል እና የቆዬ እሴት ነው ብለዋል። የበጎነት ባሕልን ማጠናከር እና ለሰው ልጆች ክብር መስጠት የብልጽግና ጉዞ አንደኛው አካል መኾኑን ገልጸዋል። የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ባለፉት ዓመታት በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።

ቤት የሌላቸውን ቤት እንዲኖራቸው፣ ቤታቸው ያረጁባቸው እንዲታደሱላቸው ተደርጓል ነው ያሉት። ባለፉት ዓመታት አዲስ ቤት በመገንባት እና በመጠገን ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማስረከባቸውን ገልጸዋል። በዘንድሮው የበጎ አድራጎት ሥራ የተሻሉ ቤቶች እንደሚሠሩ እና የቤት ዕቃም እንደሚያሟሉ ተናግረዋል።

የጭቃ ቤቶችን ሳይኾን የተሻሉ ቤቶችን እንደሚሠሩም ገልጸዋል። የመረዳዳት እሴት ከፍ እያለ መጥቷል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሕዝብን አስተባብረን የጀመርነውን እናሳከዋለን ነው ያሉት። የበጎነት ባሕላችንን የበለጠ እያጠናከርን መሄድ መቻል አለብንም ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የበጎ ፈቃድ ሥራ በአማራ ክልልም ኾነ እንደ ሀገር ሲተገበር መቆየቱን ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከማኅበረሰባችን እሴት የመነጨ ነው ብለዋል። ራስን በራስ የመቻል ሂደቶችን ስኬታማ የምናደርግበት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና በአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ነው ብለዋል። በክልሉ ከ8 ሺህ በላይ ቤቶችን ለማልማት በዕቅድ መያዙን ገልጸዋል። ልማቱን ለማሳካት ሃብት የማሠባሠብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

እርስ በእርስ የመረዳዳት ባሕል ያለው ሕዝብ አለን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ያለንን የመረዳዳት ባሕል በማቀናጀት መጠቀም አለብን ብለዋል። መንግሥት በመደበኛ ከሚሠራቸው ሥራዎች በተጫማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን መደገፍ ይገባል ነው ያሉት።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን በልዩ ትኩረት መደገፍ ካልተቻለ በመደበኛው ብቻ መደገፍ እንደማይቻል ነው የተናገሩት። በባሕርዳር ከተማ ለሌሎች ከተሞች በአርዓያነት የሚጠቀስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

“በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች መድረስ መንግሥታዊ ብቻ ሳይኾን ሞራላዊ ግዴታም ነው” ብለዋል። ሚዲያዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ በትኩረት እንዲሠሩም ጠይቀዋል። የአረንጓዴ አሻራ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በቅንጅት መሠራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።

Previous articleችግኝ በመትከል የአየር ንብረትን እና ሥነ ምኅዳርን መቆጣጠር ይገባል።
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን የአቅመ ደካሞችን እና ቤት በመጠገን እና በአዲስ በመሥራት የዜጎችን ሕይዎት የመታደግ ሥራ እየተሠራ ነው።