ችግኝ በመትከል የአየር ንብረትን እና ሥነ ምኅዳርን መቆጣጠር ይገባል።

34

ገንዳውኃ፡ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ አፍጥጥ ቀበሌ ተጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ፣ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ እና የቀበሌ መሪዎች እንዲሁም አጋር አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቡ ከችግኝ ተከላ ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመሥራት እና በማደስ እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ችግኞች አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጣር እና የደን ሃብትን ለመጨመር አይነተኛ ሚና አንዳላቸው ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ አስፈላጊውን ክትትል እና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በዞኑ ባሉ ከተሞች እና ወረዳዎች እንዲሁም ቀበሌዎች ላይ የተጀመረ መኾኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም በዞኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በዞኑ ባሉ ከተማ እና ወረዳዎች በአንድ ጀንበር ከ59 ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ኀላፊው ተናግረዋል።

ችግኝ መትከል ሥነ ምኅዳሩን ከመቆጣጠር ባለፈ የአፈር ለምነትን ለመጨመር ብሎም ምርት እና ምርታማነትን የተሻለ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሙላው በየነ የተዛባውን የአየር ሁኔታ ለማስተካከል ችግኝ መትከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የሀገርን ሰላም መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ኮሎኔል ሙላው በየነ አሳስበዋል።

ማኅበረሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በባለቤትነት መንከባከብ እና መኮትኮት እንዳለበት ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት ከተተከለው 642 ሺህ በላይ ችግኝ 474ሺህ በላይ ችግኝ መጽደቁን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን።

Previous article“የበጎ ፈቃድ ሥራው ከችግሬ አውጥቶኛል” ቤታቸው የተጠገነላቸው እናት
Next article“በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች መድረስ መንግሥታዊ ብቻ ሳይኾን ሞራላዊ ግዴታም ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ