
ደሴ፡ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ መርሐግብር ተጀምሯል።
ወይዘሮ አሚናት አሊ በተሁለደሬ ወረዳ 02 ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ቤታቸው በክረምት ለዝናብ በበጋ ደግሞ ለፀሐይ የተጋለጠ በመኾኑ ለከፍተኛ ችግር ሲዳረጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በተለይም በክረምት ዝናቡን መቋቋም ስለማይችሉ ከጎረቤት እስከመጠለል መድረሳቸውን ይናገሉ።
አሁን ግን የወረዳው ወጣት እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ባስጀመረው የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎፍቃድ አገልግሎት ቤታቸው በአዲስ መልክ እየተሠራላቸው ይገኛል። ለዚህም ወይዘሮ አሚናት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
በክረምት በጎ ፍቃድ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አሚኮ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገልጸዋል።
በ2016 የክረምት በጎ ፍቃድ በርካታ የወረዳውን ወጣቶች እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን የተሁለደሬ ወረዳ ወጣት እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀሚድ አወል ለአሚኮ ተናግረዋል።
በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድም ከ17 በላይ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ከ64 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ እና ከ18ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኞችን ለማሳተፍ በዕቅድ መያዙን አቶ ሀሚድ ገልጸዋል።
በክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ከባለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድም ከ820 ሺህ በላይ ኅብረተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚሠሩ እና ለዚህም ከ940ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ሥራው ከ834 ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥት ሊያወጣ የሚችለውን ገንዘብ እንደሚያስቀር ምክትል አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል።
ከክረምት በጎ ፍቃድ ጎን ለጎን የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ ዞኑ ሥራዎችን እንደሚሠራም አቶ አሊ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን